በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን ህፃን ሄቨንን ጉዳይ እንደሚከታል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ
ሚኒስቴሩ በተፈፀመው ወንጀል ዙሪያ የተሰጠውን ዉሳኔ አስመልክቶ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚኬድበት አግባብ ትክክል አይደለም ብሏል
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር “ወንጀለኛውን በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ብቻ መቅጣቱ እጅግ ያነሰ ነው” ብሏል
በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን ህፃን ሄቨንን ጉዳይ እንደሚከታል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የ7 ዓመቷ ህፃን ሄቨን በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍራ እንደተገደለች ወላጅ እናቷ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስትናር መሰማቱን ተከትሎ ጉዳዩ መነጋሪያ እና በርካቶች ያስቆጣ ሆኗል።
ህጻኗን በመድፈር ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት የቀረበው ግለሰብም የ25 ዓመት እስራት የተፈረደበት ቢሆንም፤ ቅጣቱን ለማቅለል እና ለማስለቀቅ ይግባኝ እንደተጠየቀበት እንደሆነም ነው የህጻኗ እናት የተናገረችው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫው፤ የህፃናትን መብት በማስጠበቅ ረገድ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ተግባራትን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሆነ አስታውቋል።
በአሁን ወቅት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን ህፃን ሄቨን በተመለከተ ለደረሰው ዘግናኝ የሆነ ኢሰብአዊ ወንጀል በተመለከተ ሚኒሰትር መስሪያ ቤቱ የተሰማውን ሀዘን የገለጸ ሲሆነ፤ እንዲህ አይነት የህፃናት ጥቃት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በፅኑ እንደሚያወግዝም አስታውቋል።
“በተፈፀመው ወንጀል ዙሪያ የተሰጠውን ዉሳኔ አስመልክቶ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚኬድበት አግባብ ትክክል አይደለም” ያለው ሚኒስቴሩ፤ “ከፍትህ አካላት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራት እና እንደሚከታለው ገልጿል።
የሴቶች እና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኢርጎጌ ተሰፋዬ በጉዳዩ ላይ በማህበራዊ ትስስር ገጻው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በቅርቡ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን ህፃን ሄቨን በተመለከተ ለደረሰው ዘግናኝ ኢሰብአዊ ወንጀል በሚኒሰትር መስሪያ ቤታችንና በራሴ ስም የተሰማንን ሀዘን እየገለፅሁ” ብለዋል።
“ጉዳዩ ዉሳኔ የተሰጠበት ቢሆንም ይግባኝ ለመጠየቅ የሚኬድበት አግባብ ትክክል ባለመሆኑ ከሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ጋር በመሆን ጉዳዩን የምንሰራበትና የምንከታተለው እንደሆነ እንገልፃለን” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ትናነት ባወጣው መግለጫው፤ በባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በኩል ድርጊቱ መፈፀሙን መረጃ እንዳገኘ እና ጉዳዪን ካወቀበት ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በቅርበት ሲከታል መቆየቱን አስታውቋል።
ፍርድ ቤት ላይ በመገኘትም ችሎቱን በቅርበት ስንከታተል ነበርን ያለው ማህበሩ፤ በመጨረሻም ድርጊት ፈፃሚው በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዉሳኔ ሊያሳልፍ ማቻሉን አስታውቋል።
“ይሁን እንጂ ወንጀለኛው የፈፀመው አሰቃቂና ተደራራቢ ወንጀል አሳዛኝና አሰቃቂ ነው ያለው” ማህበሩ፤ በተለይ በህፃናት ላይ እንደዚህ ዓይነት ወንጀል ሲፈፀም እጅግ የሚያስከፋና የሚያስቆጣ ነው፤ የስር ፍርድ ቤትም ወንጀለኛውን በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ብቻ መቅጣቱ እጅግ ያነሰና የግድያ ወንጀሉ ብቻ በራሱ የእድሜ ልክ ወይም የሞት ፍርድ ሊያስቀጣው ሲገባ ስር ፍርድ ቤቱ በ25 አመት ፅኑ እስራት ብቻ ውሳኔ ሰጥቶ ማለፉ ስህተት ነው” ብሏል።
“ከዚህም በላይ ይህ በሆነበት ሁኔታ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የህክምና ማስረጃ ለማጣራት በማለት ያስቀርባል የሚል ትዕዛዝ በመስጠት ለጥቃት አድራሽ የማይገባ ተስፋ መስጠቱ እጅግ አሳዛኝ ነው” ብሏል ማህበሩ በመግለጫው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ይህንን የህፃን ሄቨንን ጉዳይ የይግባኝ ሂደቱን እየተከታተለ እንደሚቆይና ህፃን ሄቨን ፍትህ እንድታገኝ ማኅበሩ የበኩሉን ጥረት እያደረገ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።