የህወሓት “ሃላፊነት የጎደለው ተግባር” በተናጠል የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ ዳግም እንዲያጤነው እያስገደደው መምጣቱን መንግስት አስታወቀ
ለህገ ወጥ ድርጊቱ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪውን ቡድን የመጠየቂያ ጊዜው አሁን ነው ሲልም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል
ከአሁን በኋላ በአጎራባች ክልሎች ላይ አዲስ ጥቃት ተፈጽሞ የዜጎች ህይወት እንዲመሰቃቀል እንደማይፈቅድም ገልጿል
“አሸባሪው ህወሃት ከትግራይ ክልል አልፎ በአጎራባች ክልሎች ላይ ተጨማሪ የጥቃት ድርጊት እንዲፈጽምና የዜጎችን ህይወት እንዲያመሰቃቅል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ያሳለፈው የኢትዮጵያ መንግስት አይፈቅድለትም” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው አሸባሪው ህወሃት እየፈጸመ ባለው ጥቃት የተነሳ የታለመለትን ዒላማ ሊያሳካ እንዳልቻለ አመልክቷል።
ቡድኑ በከፈተው ጥቃት ከአፋርና አማራ ክልሎች ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉና በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓል።
ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት የተኩስ አቁም ውሳኔውን እንዳከበረ እንደሚገኝ ገልጾ፤ አሸባሪው ቡድን እየፈጸመ ያለውን ሰብዓዊ ግፍ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለው አመልክቷል።
በመሆኑም መንግስት በአሸባሪው ህወሃት ተጨማሪ ጥፋትና ግፍ እንዲፈጸምና ዜጎች ኑሯቸው እንዲመሰቃቀል የማይፈቅድ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።
የቡድኑ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት የመንግስትን ትዕግስት ከመፈታተን አልፎ ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል የተወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ ሃሳብ ለመለወጥ እያስገደደው እንደሆነም አመልክቷል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች እፍረት በማያውቀው አሸባሪው ህወሃት አማካኝነት ህይወታቸውን እንዳጡ የጠቀሰው መግለጫው፤ ህጻናቱን የጥይት ማብረጃ እያደረጋቸው እንደሚገኝም ገልጿል።
በትግራይ ሰላም እንዲሰፍን በመንግስት በኩል ሰፊ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሶ፤ በተንኳሽነቱ የሚታወቀው አሸባሪው ህወሃት በክልሉ ያደፈረሰውን ሰላም ወደአጎራባች ክልሎች በማስፋፋት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ እያደረገ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።
በትግራይ እና አሸባሪው ቡድን ግፍ በፈጸመባቸው አፋርና አማራ ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ አሸባሪው ህወሃት ዜጎች ድጋፍ እንዳያገኙ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰና እያደናቀፈ እንደሚገኝ አመልክቷል።
የተናጠል የተኩስ አቁሙን ችላ በማለት ግፍ እያደረሰ የሚገኘውን አሸባሪ ቡድን የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው የጠየቀው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ህገ ወጥ ታጣቂው አሸባሪው ህወሃት በግልጽና በድብቅ ከሚፈጽመው የሽብርና የወረራ ድርጊት እንዲታቀብ አሳስቧል።
ቡድኑ በአፋርና በአማራ ክልሎች በከፈታቸው ጥቃቶች የሰላም አማራጭ እንዲዘጋ እያደረገ እንደሆነም አመላክቷል።
የሰላም አማራጩ ከተዘጋ ደግሞ የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ የሞራል፣ የህግና የፖለቲካ ግዴታ ያለበት የፌዴራል መንግስቱ የመከላከል አቅሙን ለመጠቀም እንደሚገደድም ማስገንዘቡን ኢዜአ ዘግቧል።