የአማራ ልዩ ሃይል ከሽሬ እና አካባቢው መውጣቱን መከላከያ አስታወቀ
በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ከህወሃት የትጥቅ መፍታት ሲጀምር "የውጭ ሃይሎች" ከትግራይ ይወጣሉ ይላል
ህወሃት በአጉላ ካምፕ የመጀመሪያ ዙር ከባድ መሳሪያዎችን ማስረከቡን ተከትሎም የአማራ ልዩ ሃይል ከሽሬ ወጥቷል ተብሏል
የአማራ ልዩ ሃይል ከሽሬ እና አካባቢው እንዲወጣ መደረጉን የመከላከያ ሰራዊት ገልጿል።
መከላከያ ሰራዊት በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ "በሽሬ እና አካባቢው በግዳጅ ላይ የቆየው የአማራ ልዩ ሀይል ሽኝት ተደርጎለታል" ብሏል።
የአማራ ልዩ ሃይል በሽሬና አካባቢው በግዳጅ ላይ ተሰማርቶ ስለመቆየቱ ከዚህ በፊት በመንግስት ሲነገር አልተደመጠም።
የመከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው የአማራ ልዩ ሃይል ከሽሬ የወጡት በሰላም ስምምነቱ መሰረት መሆኑን ጠቁሟል።
ከሁለት ወራት በፊት የፌዴራል መንግስትና የህወሃት አመራሮች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በደረሱት የሰላም ስምምነት "የውጭ ሃይሎች" ከትግራይ የሚወጡበት ሁኔታን ለማመቻቸት ተስማምተዋል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ የፌደራል መንግስቱ እና የህወሃት ወታደራዊ አመራሮች በኬንያ ናይሮቢ በተፈራረሙት ሰነድም ይሄው ነጥብ ተሰምሮበታል።
በስምምነቱ ህወሃት ከባድ መሳሪያዎችን ማስረከብ ሲጀምር የውጭ ሃይሎችም ከትግራይ እንዲወጡ እንደሚደረግ ተጠቅሷል።
በዚህም መሠረት ህወሃት ከትናንት በስቲያ የመጀመሪያ ዙር ከባድ መሳሪያዎችን አስረክቧል።
ህወሃት ከመቀሌ በ36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አጉላ ካምፕ ነው የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች በተገኙበት ከባድ መሳሪያዎችን ያስረከበው።
ይህን ተከትሎም "የኢትዮጵያ መንግስት በሽሬ እና አካባቢው ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ተሠልፎ ሀገራዊ ተልዕኮን ሲፈፅም የነበረው የአማራ ክልል ልዩ ሃይል በስምምነቱ መሠረት ከቀጠናው እንዲወጣ አድርጓል" ብሏል የመከላከያ መግለጫ።
የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ እና የዕዝ አመራሮች በተገኙበት የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ሽኝት እንደተደረገለትም መከላከያ ሰራዊት ገልጿል።
የልዩ ሃይሉ አመራሮች "እስካሁን የከፈልነው ዋጋ ለጋራ ሠላማችን ስንል ነውና በመንግስት ትዕዛዝ መሠረት በተደረሰው የሠላም ስምምነት ሃይላችንን ከሽሬ እና አካባቢው እያሥወጣን ነው" ማለታቸውም ተገልጿል።