የኢትዮጵያ መንግስት ማንነትን መሰረት ያደረገ እስር አለመኖሩን ገልጿል
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአዲስ አበባ ህጻናትንና አዛውንቶችን ጨምሮ የትግራይ ተወላጆችን ኢላማ ያደረገ የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው የሚለውን ማንኛውንም ሰው ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር እንደሚያደርግ የገለጸው መንግስት ማንነትን መሰረት ያደረገ እስር አልተፈጸመም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ተወላጆች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ እስር መኖሩን መግለጹ ይታወሳል፡፡
አብዛኞቹ በእስር ላይ ያሉት ሰዎች ክስ እንዳልቀረበባቸውና የጠበቃ ድጋፍ ማግኘት አልቻሉም ያለው አምነስቲ፤ የጅምላ እስሩ በትግራይ ተወለጆች ላይ ፍርሃት እንዲነግስ ማድረጉን ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከ10 ቀናት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ ጀምሮ እስሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል አምነስቲ፡፡
እስሩ እየተካሄደ ያለው በቤት ለቤት ፍተሻ ነው ያለው አምነስቲ ከታሰሩት መካከል የመንግስት ሰራተኞች፣ቄሶች እና የህግ ጠበቆች ይገኙበታል ብሏል፡፡ አምነስቲ እንዳለው በአዲስ አበባ የሚገኙት ፖሊስ ጣቢያዎች ስለተጨናነቁ፣ እስረኞቹ በወጣት ማእከላትና መደበኛ ባልሆኑ ማእከላት ይገኛሉ፡፡
የአምስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ዳሬክተር ዲፕሮዜ ሙቸና “በእስር ላይ የሚገኙት ሰዎች አልተከሰሱም ወይም ወደ ፍርድ ቤት አልቀረቡም፤ምናልባትም በብሄር ማንነታች ብቻ ኢላማ ተደርገው”ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ለቤተሰቦች የታሰሩት ሰዎች ያሉበትንና የደህንነታቸውን ሁኔታ ያለምንም መዘግየት ማሳወቁን ማረጋገጥ አለበት ብሏል፡፡
አምነስቲ ጥቂት ታሳሪዎች ቤተሰቦችና ጓደኞች የተወሰነና መደበኛ ያልሆነ ታሳሪዎችን የማግኘት እድል ቢኖራቸውም አብዛኞቹ ጠበቃ እንዳያገኙ መከልከላቸውን ጠቅሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) በአዲስ አበባ ከታሰሩት ሰራተኞቹ በተጨማሪ በአፋር ክልል ሰመራ 72 የተመድ ተሽከርካሪ ሹፌሮች መታሰራቸውንና አግባብ አለመሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተመድ ሰራተኛ በመሆን ብቻ የታሰረ አለመኖሩን ህግ የተላለፈ የየትኛውም አለምአቀፍ ወይም ቀጠናዊ ድርጅት ሰራተኛ ከተጠያቂነት አያመልጥም የሚል መልስ ሰጥቷል፡፡