የህወሃት ታጣቂዎች በቆቦ “ቤት እያንኳኩ” ሰው እየገደሉ መሆናቸውን የወረዳው አስተዳዳሪና ነዋሪዎች ተናገሩ
ኢሰመኮ በቆቦ ከተማና አካባቢዋ የደረሰው ግድያ እንደሚያሳስበው ገልጾ ነበር
ማንነታቸው የታወቁ ከ60-70 የሚሆኑ አስከሬኖች በ8 ቤተክርስቲያናት ሲቀበሩ ሌሎቹ ባሉበት መቀበራቸውን ነዋሪው ተናግረዋል
የህወሃት ታጣቂዎች በራያቆቦ ወረዳ የገጠር ቀበሌዎችና በቆቦ ከተማ ባለፈው ጷጉሜ አራት እና አምስት በፈጸሙት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ግድያው የተጀመረው ገደባዩ በምትባል አንድ የገጠር ቀበሌ፣የህወሃት ታጣቂዎች አርሶ አደሩን መሳሪያ አምጡ እያሉ ማስፈራራታቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት መሆኑን ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ሸሽቶ ያለመጠ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል፡፡
- የአማራ ክልል መንግስት ህወሃት በሰነዘረው ጥቃት በክልሉ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል አለ
- መንግስቴን ያለአግባብ የሚገስጸው አለምአቀፉ ማህበረሰብ ህወሃትን በጥብቅ ማስጠንቀቅ አልቻለም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ
- በትግራይ ያለውን ሰብዓዊ አቅርቦት ለማቀላጠፍ በሚል የፍተሻ ጣቢያዎች ቁጥርን መቀነሱን መንግስት አስታወቀ
ነዋሪው እንዳለው ታጣቂዎቹ፣ ከገጠር ከተመለሱ በኋላ ቆቦ ከተማ በመግባት መንገድ ላይ ያገኙትን ሁሉ መግደል መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ከቤት እያስወጡና አረም ውለው በመመለስ ላይ የነበሩ ገበሬዎችን ገድለዋል ሲል ነዋሪው ገልጿል፡፡
ባካባቢው ባሉ 8 ቤተክርስቲያናት ከ60-70 አስከሬኖች ተቀብረዋል ያሉት ነዋሪው ከ600-800 ሰዎች ጷጉሜ አራትና አምስት ተገድለዋል ብሏል ነዋሪው፡፡
ነዋሪው በሁለተኛ ቀን ከቆቦ ከተማ በማሽላ ውስጥ ተደብቆ በማምለጥ አሁን ደሴ ተፈናቃይ ካምፕ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ ነገርግን ግድያው አሁንም መቀጠሉን የገለጸው ነዋሪ ቆቦ ከተማ የሚገኙት ቤተሰቦቹ ጉዳይ እንደሚያስጨንቀው ተናግሯል፡፡
“በጅብ የተበሉ አስከሬኖች አሉ፤ የተቀሩትን መታወቂያቸው እየታየ ቤተክርስቲያን መቀበራቸውን እና መታወቂያ የሌላቸው ባሉበት መቀበራቸው“ነዋሪው ገልጸዋል፡፡ነዋሪው እንደገለጸው በአንድ ቤት ውስጥ ብቻ አራት የቤተሰብ አባላትና ሶስት ሸሽተው ገብተው የነበሩ በድምሩ 7 ሰዎች ተገድለዋል፡፡በረሃብና በጦርነት መሀል ላለው ህዝብ መንግስት ሊደርስለት ይገባል ሲል ጠይቋል፡፡
ሌላኛው የራያ ቆቦ ነዋሪ አቶ ይርጋለም ታደሰ በእግር ከቆቦ አካባቢ ወደ ሰላም ቀጠና እስከ ድሬ ሮቃ ድረስ ከሞት አምልጠው የመጡትን ሰዎች ማናገሩንና ራያ ቆቦ ላይ ንጹሃን በአሰቃቂ ሁኔታ ብዙ ሰዎች መገደላቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል፡፡
“የነበረው ሁኔታ በጣም አስከፊ ነው፤ መንግስት በሰጠው መግለጫ ጁንታዎቹ ከአፋር ክልል ወጡ ብሎ ነበር፤ ይህንንም ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ተረድተውት ነበር” ይላል አቶ ይርጋለም፡፡
“ነገር ግን ከአፋር ወጥተው ሳይሆን ሙሉ ትኩረታቸውን በመቀየር ወደ ሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ አድረገው ነበር፡፡ ራያ አካባቢ ያለው ሕዝብ፣ ፋኖና ጢነኛ ከባድ መስዋዕትነት በመክፈል አካባቢዎቹን ነጻ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ነገር ግን ከአፋር ክልል ከባድ መሳሪያ የያዙ የጁንታው ኃይሎች በመምጣታቸው የራያን ሕዝብ ላይ ለመበቀል ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አድርሰዋል፡፡ “
“መንግስት ፍትሐዊ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ ለትግራይ ገበሬ ያዘነ መንግስት ለወሎ ገበሬ፤ ለራያ ገበሬ፤ ሊያዝን ይገባል“ በማለት ይርጋለም በምሬት ተናግሯል፡፡
የራያቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ አሽብር ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ከቦታው የተሟላ መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ሰው እየተገደለና እየተደበደበ መሆኑን መረጃ እንደደረሳቸው ገልጸዋል፡፡
እሳቸው በረሃ መሆናቸውን የተናገሩት አስተዳዳሪው በራያቆቦ የህወሃት ታጣቂዎች “ቤት እያንኳኩ” ሰው በመግደል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በረሃ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ መንገሻ አሁን በተወሰኑ ቀበሌዎች የሽምቅ ውጊያ እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በቆቦ ከተማና በዙሪዋ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች በንጽሃን ላይ ግድያ መፈጸሙ እንዳሳሰበው ገለጾ ነበር፡፡ ኢሰመኮ የህወሃት ታጣቂዎች ቤት ለቤት በመዞር ንጹሃንን መግደሉንና መሰረተልማት ማውደሙን ሪፖርት እንደደረሰው መግለጹ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ የህወሃት ታጣቂዎች ሴቶችን፤ህጻናቶችን ጨምሮ ንጽሃን በአፋርና በአማራ ክልል በሀይል ተፈናቅለዋል፤ ኑሯቸው ተመስቃቅሏል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሃት አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች ሆንብሎ በህወሃት ማውደሙን ጠቅሰዋል፡፡ የፌደራል መንግስት ህወሃት ሀገር የማፍረስ ድርጊት ፈጽሟል በማለት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት አስፈርጆታል፡፡
የፌደራል መንግስት ግጭቱን በውይይት ለመፍታት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ጦሩን ክትግራይ ክልል ቢያስወጣም፤ ግጭቱ ሊቆም አልቻለም፡፡ በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ወደ አፋርና አማራ ክልል ሊስፋፋ ችሏል፡፡
የፌራደል መንግስት ተኩስ አቁም የተፈለገውን ለውጥ ባለማምጣቱ፤ መከላከያና የክልል ልዩ ኃይሎች በህወሃት ሃይሎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ አዝዞ፤ጦርነቱ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ አለምአቀፍ ማህበረሰብ የፌደራል መንግትና ህወሓት ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ጫና በማሳደር ላይ ናቸው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ከሚሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በግለሰቦች ላይ ማእቀብ መጣል የሚያስችል ትእዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሰብአዊ ድጋፍ እንዲፈልጉ እና ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።