የታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ግለ ታሪክ የያዘ የአረብኛ መጽሃፍ ተመረቀ
መጽሃፉ በተለያዩ ዘርፍ ለኢትዮጵያ አስዋጽኦ ያበረከቱ 50 ኢትዮጵያውያን ታሪክ በውስጡ ይዟል
ደራሲና ጋዜጠኛ አንዋር ኢብራሂም “መጽሃፉ ኢትዮጵያን ከአረቡ ዓለም ጋር ለማስተዋወቅ ይረዳል” ብሏል
የታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ግለ ታሪክ የያዘ “ሸክሲያት ኢትዮጵያ” የተሰኘ የመጀመሪያው የአረብኛ መጽሃፍ ተመርቆ ለብባብ መብቃቱ ታውቋል።
በደራሲና ጋዜጠኛ አንዋር ኢብራሂም የተዘጋጀው መጽሃፉ በተለያዩ ዘርፍ ለኢትዮጵያ አስዋጽኦ ያበረከቱ 50 ኢትዮጵያውያን ታሪክ በውስጡ ይዟል።
በመጽሃፉ በስፖርት፣ በፖለቲካ፣ በሙዚቃ፣ በስነ ጥበብ እና በሌሎች ዘርፎች ስመ ጥር የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ በውስጡ የያዘ መሆኑ ተነግሯል።
በመጽሃፉ ምርቃት ላይ የተገኙ የተለያዩ ግለሰቦች ስለ ኢትዮጵያ በአረብኛ የተጻፉ መጽሃፍቶችን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንዲህ አይነት መጽሃፎች መዘጋጀታቸው የኢትዮጵያን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል እና በተለያዩ ዘርፎች ከአረቡ ዓለም ጋር ለማስተዋወቅ ይረዳል ብለዋል።
የመጽሃፉ አዘጋጅ ደራሲና ጋዜጠኛ አንዋር ኢብራሂም በምረቃው ላይ ባደረገው ንግግር፤ መጽሃፉን ለማዘጋጀት 4 ዓመታትን እንደፈጀበት አስታውቋል።
“ሸክሲያት ኢትዮጵያ” የተሰኘው መጽሃፍ አሁን ላይ የ50 ኢትዮጵያውያንን ታሪክ የያዘ መሆኑን ጠቅሶ፤ በቅርቡም የተጨማሪ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ የያዘ ቁጥር ሁለት መጽሃፍ ለንባብ እንደሚያበቃ አስታውቋል።
በአረቡ ዓለም በተለይም በሚዲያው ዘርፍ አንጻር ካለው ልምድ አንጻር ሲናገርም፤ በብዛት ስለ ኢትዮጵያ አውንተዊ ነገር እንደማይነገር እና ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዘገባዎችን ለመዘጋጀት ሲፈለግ በአረብኛ የተጻፉ ታሪኮችን ማገኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ታነግሯል።
እንዲህ አይነት መጽሃፍ በአረቡ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ መልካም ገጽታን ለመገንባት ጠቃሚ መሆኑንም አስታውቋል።
ደራሲና ጋዜጠኛ አንዋር ኢብራሂም ከዚህ ቀደም ሁለት መጽሃፍቶችን ለንባብ ያበቃ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቅርሶች ዙሪያ የጻፈው የመጀመሪያ መጽሃፉን ከዓመጻ በፊት በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ታትሞ ለገበያ መቅረቡ ይታወሳል።