በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው የእስከዳር ግርማይ መጽሃፍ “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው” ስለሚለው ምላሽ አለው
እስከዳር ግርማይ ነዋሪነቷን ባህሬን ያደረገች ኢትዮጵያዊት ስትሆን አዲስ መጽሀፍ ጽፋ ከአንድ ወር በፊት ለንባብ አብቅታለች፡፡ “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው” በሚል ርዕስ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ደራሲዋ ገልጻለች፡፡
ደራሲ እስከዳር ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረገችው ቆይታ እንደገለጸችው መጽሐፉ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ “ኢትዮጵያዊ ማነው” በሚል ርዕስ ለምን እንደጻፈችው ስታብራራም “የኢትዮጵያዊ ሀገርን ስፈልግ አይቸው ነው፤ ሀገሩ ለጠፋበት ሰው ነው የጻፍኩት” ስትል ትናገራለች፡፡ ሆኖም በአረብ ሀገራት የቤት ሰራተኛ ነበርኩ የምትለው እስከዳር እስካሁን ለጥያቄው መልስ አላገኘችም፡፡
ይህንን መጽሀፍ የጻፈችው በግል በደረሰባት ጉዳይ መሆኑን የገለጸችም ሲሆን ከተለያዩ ብሔሮች መገኘቷ ለመጻፍ መነሻ እንደሆናት አንስታለች፡፡
“እኔ ምናብ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ እና አለች የሚሉኝ ኢትዮጵያ ሲለያዩብኝ ነው “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው” ያልኩት” ስትልም ታስቀምጣለች፡፡ ምንም እንኳን መነሻዋ የግል ቢሆንም ሌሎችም ጥያቄ ያላቸው አካላት እንደሚኖሩ ገልጻለች፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ላይ እንደዚህ አይት ነገር መኖሩንና ሃሳብ ለማንሸራሸር ይጠቅማል በሚል መጻፏንም ነው ደራሲዋ የምትገልጸው፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያዊ የሚለው ላይ እንዲነጋገሩ ዕድል ይሰጣል ብላ እንደምታምንም ተናግራለች፡፡
“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው” የሚለው የእስከዳር መጽሃፍ በ20 ታሪኮች የተዋቀረ ነው፡፡ በታሪኮቹ የተለያዩ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ ሆኖም በርዕስነት ለቀረበው ጥያቄ አንደኞቹም ምላሽ አይሰጡም፡፡
ደራሲዋ ይህ ለምን እንደሆነ ስትገልጽ “መልሱን አብረን ነው የምንፈልገው” ትላለች፡፡ ሰው ከዘሩና ከብሔሩ ሳይጣላ ኢትዮጵያዊ መሆን እንደሚችል አምናለሁ የምትለው ደራሲዋ፤ ብሔር አትጥሩ የሚሉትን ሃሳብም እንደማትቀበል አንስታለች፡፡ ሀገራዊ ማንነትንና የብሔር ማንነትን አብሮ ማስኬድ እንደሚቻልና ይህንንም ማክበር እንደሚገባ አንስታለች፡፡ እስከዳር በቀጣይ ሌሎች መጽሐፎችን ለመጻፍ ማቀዷን ገልጻለች፡፡
መጽሀፉ እና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ
መጽሐፉ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ እንደሚያሳይ የምታነሳው እስከዳር በሀገር ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ የሚሆነው ችግሩን ማመን እንደሚመስላት ገልጻለች፡፡ ምን ችግር አለ ብሎ ችግርን አምኖ መቀበል እንደሚያስፈልግ የምታነሳው ደራሲዋ ስለአንድነት ስናወራ “እውነት አንድ ነን ወይ?” የሚለውን መጠየቅና ምላሽ መስጠት ይገባል ትላለች፡፡
“የሆነ አንድ ክልልን ትተህ አንድነት እያልክ ማውራት አትችልም ፤ ያ የታለ፤ ያኮረፈም ቢሆን የሞተም ለምን ይሞታል ብለን መጠየቅ አለብን” ስትልም ነው የምትገልጸው፡፡
የአንዱ ህመም የሌላው ህመም እንዲሆን ማድረግ ይገባል ያለችው እስከዳር በሀገር ስም ብሽሽቅ ውስጥ መግባት እንደማይገባ ታነሳለች፤ በድርሰትና በኪነ ጥበብ ውስጥ ያሉ ሰዎችም “የሕዝብ ነን” ሲሉ “የሁሉም መሆን” እንዳለባቸው በመጠቆም፡፡
የቤት ሰራተኝነት ፈተናን ማሸነፍ
በርካታ ኢትዮጵያዊ ሴቶች በአረብ ሀገራት በቤት ሰራተኝነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሴቶችም ብዙ ጊዜ ስለመጎዳት፣ ስከለችግር፣ ከፎቅ ስለመወርወር፣ ስለመደፈርና ስለመገደል እንደሚያወሩ ታነሳለች፡፡ ለዚህ የችግርና የተስፋ መቁረጥ መንፈስ ብዙ አካላት ተጠያቂ ቢሆኑም ቤተሰብም ራሱ ተጠያቂ መሆን እንዳለበትና በዚህ ዙሪያ ብዙም እንዳልተወራ ታነሳለች፡፡ እንደ እስከዳር ገለጻ ተስፋ ባለመቁረጥ ጥረት ከተደረገ ፍላጎትን ማሳላት ይቻላል፡፡ እኔ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን እችላለሁ ስትል ነው የምትገልጸው፡፡