የፌዴራል መንግስት “እንዳልተካሔደ ይቆጠራል” ያለው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው
“በሚቀጥለው የፓርላማም ሆነ ሌሎች ምርጫዎች ካልተሳተፈ ህወሓት ተቀባይነት አይኖረውም” ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
ምርጫውን “የጨረቃ ምርጫ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምርጫው ትርጉም እንደሌለው ገልጸዋል
የፌዴራል መንግስት “እንዳልተካሔደ ይቆጠራል” ያለው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው
የትግራይ ክልል ለሚያካሒደው 6ኛው ክልላዊ ምርጫ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መራጮች ድምጽ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መቐለን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ እየተሰጠ መሆኑን በፎቶ ማስረጃ አስደግፎ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በአድዋ ተገኝተው ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
ክልሉ ለሚያሔደው 6ኛው ክልላዊ ምርጫ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የምርጫ ካርድ ማውጣቱን የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን መግለጹ ይታወቃል፡፡ ድምጽ ለመስጠት 2,672 የምርጫ ጣቢያዎች መቋቋማቸውም ተገልጿል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን ማካሔድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው እንዲራዘም መወሰኑ ይታወቃል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ስጋት አለመሆኑ በዓለም ጤና ድርጅት እና በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር ማረጋገጫ ከተሰጠ በኋላ ከ9 ወር እስከ 1 ዓመት ባለው ጊዜ ዉስጥ ምርጫው እንዲካሔድ ምክር ቤቱ በወቅቱ ወስኗል፡፡
የትግራይ ክልል ዛሬ የሚያካሒደውን ምርጫ በተመለከተ ከጥቂት ቀናት በፊት ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሔደ አስቸኳይ ስብሰበባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው ኢ ሕገመንግሥታዊ መሆኑን በድጋሚ አንስቶ መክሯል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት በክልሉ የሚካሔደው ምርጫ እንዳልተካሔደ እንደሚቆጠር በመግለጽ መንግሥት ለምርጫው እውቅና እንደማይሰጥ ዉሳኔም አሳልፏል፡፡
አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ በትግራይ የሚካሔደውን ምርጫ “የጨረቃ ምርጫ ነው” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ “የጨረቃ ምርጫ ልክ እንደ ጨረቃ ቤት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የጨረቃ ቤት የሚሰሩ ሰዎች ህገ ወጥ መሆናቸውን ስለሚያውቁ ተኝተው አያድሩም” በማለት የክልሉን ምርጫ ህገወጥነት ከዚሁ ጋር በማነጻጸር አብራርተዋል፡፡
ምርጫው ከመካሔዱ በፊትም ይሁን ከተካሔደ በኋላ ህወሓት ክልሉን የሚመራ መንግስት ሆኖ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡ ይሁንና ህወሓት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባሳለፈው ዉሳኔ መሰረት መንግስትነቱ የሚያበቃው አሊያም የሚቀጥለው በቀጣይ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚካሔደው ምርጫ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ አሁን የሚካሔደውን ምርጫ”የእቁብ ወይም የዕድር ስብስብ” ብለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ይህ ለእኛ ትልቅ ራስ ምታት መሆን የለበትም” በማለት ለምርጫው ትርጉም እንደማይሰጡ ሀሳባቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በሚቀጥለው የፓርላማም ሆነ ሌሎች ምርጫዎች ላይ የማይሳተፍ ከሆነ ግን “ህወሓት ተቀባይነት አይኖረውም”፡፡ በትግራይ የሚካሔደው ምርጫ እንደምርጫ መታየት እንደሌለበት በአጽንኦት በመግለጽ “ምርጫ የሚባለው በብሐየራዊ ምርጫ ቦርድ ሲመራ ብቻ ነው ፣ የዕድር ስብስብ ዉጤቱ በህግ የተሰጠውን መንግሥት የሚቃረን ካልሆነ ለዚያ ብሎ ጊዜ ማባከን ያስፈልጋል ብዬ አላስብም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ “ዉጊያ ቢያስፈልግ” ባጠረ ጊዜ ዉስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዉጊያ ግን እንደማያስፈልግ እና እርሳቸውም እንደማይደግፉ በቆይታቸው አንስተዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያየው ከትግራይ ህዝብ አንጻር መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችም በህዝቡ ላይ ከሚኖራቸው ተጽዕኖ አንጻር እንደሚለኩ ተናግረዋል፡፡ “የትግራይን ህዝብ በህዝቡ ላይ ከተደራጀው ግሩፕ የሚለይ እሳቤ ሳይኖር ግሩፑን በመጥላት እሱን ለማጥፋት በሚደረግ ጥረት ህዝቡ መጎዳት የለበትም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ ችግሮች ላሉበት የትግራይ ክልል “አንድ ጥይት ሳይሆን አንድ አፍ መሸፈኛ ፣ አንድ ጥይት ሳይሆን አንድ ታብሌት ነው መላክ ምፈልገው ፤ አንድ የዉሃ ጉድጓድ መቆፈር ነው የምፈልገው” ብለዋል፡፡ “አሁን ያለው ኃይል (ህወሐት) ጭንቅላቱ ደርቋል ፤ ኪሱ እየደረቀ ሲሔድ እያየነው ፣ ይረግፋል ለዚህ ብለን ጊዜ ማባከን አያስፈልገንም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም በቅርቡ ከአል ዐይን ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ክልሉን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሚወክሉ አባላት በፌደራል ደረጃ በሚደረገው ምርጫ እንደሚመረጡ ተናግረዋል፡፡ “ይህ ምርጫ የሚመለከተው ትግራይን ብቻ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ “ለክልል ም/ቤት ድጋሚ ምርጫ ማድረግ አይጠበቅም” ሲሉም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡