የክልሉ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሔድ ላይ መሆናቸው ተገልጿል
የትግራይ ክልል በተናጥል ለማካሔድ ላሰበው ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ተጀመረ
ሕወሀት “ታሪካዊ” ላለው 6ኛው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ነሀሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ትግራይ መጀመሩን በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። የመራጮች ምዝገባ እስከ ነሓሴ 22 ይቀጥላልም ነው የተባለው።
“የትግራይ ህዝብ በራስ ተነሳሽነትና በላቀ ዲሲፕሊን የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ መጉረፍ ጀምሯል” ሲል ፓርቲው ገልጿል።
የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በሰጠው መግለጫ ምርጫው ጳጉሜ 4 እንደሚካሔድ ይፋ አድርጓል፡፡ በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎችም በክልሉ መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉበት ዉይይት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የፌደሬሽን ምክር ቤት በህገመንግስት ትርጉም ምርጫው እንዲራዘም መወሰኑን በማስታወስ “በትግራይ ክልል ችግር የሚፈጠረው በምርጫው ሕወሀት ስልጣኑን ለሌላ ፓርቲ አሳልፎ ከሰጠ ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያ ዉጭ የፌዴራል መንግስት ምርጫው እንደማያሳስበው ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም ከሳምንት በፊት ከአል ዐይን ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ክልሉን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሚወክሉ አባላት በፌደራል ደረጃ በሚደረገው ምርጫ እንደሚመረጡ ተናግረዋል፡፡
“ይህ ምርጫ የሚመለከተው ትግራይን ብቻ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ “ለክልል ም/ቤት ድጋሚ ምርጫ ማድረግ አይጠበቅም” ብለዋል፡፡
“በፌዴራል የትግራይ ውክልና ሲፈለግ ሌላ ጉዳይ ይሆናል፤ በፌዴራል ደረጃ የሚወከሉ ሰዎች ምርጫ ይደረጋል ማለት ነው” በማለት ኮሚሽነሩ ለአል ዐይን ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በክልል ደረጃ የተቋቋመው የምርጫ ኮሚሽንም ይሁን በክልሉ የሚደረገው ምርጫ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን እና ሕገወጥ መሆኑን የፌዴራሉ መንግስት በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት ክልሉ ምርጫ ከማድረግ እንቅስቃሴው እንዲታቀብ ከማስጠንቀቁ ዉጭ የፌዴራል መንግስት ይህን ለመከላከል ስለሚወስደው እርምጃ በግልጽ ያለው ነገር ግን የለም፡፡