አቶ አንዷለም አራጌ ከመሰረቱት ኢዜማ ለምን ለቀቁ?
አቶ አንዷለም ከኢዜማ መልቀቃቸውን በገለጹበት ደብዳቤ ፥ ፓርቲው “ከስሁት መንገዱ መመለስ በማይችልበት መዳፍ ውስጥ ወድቋል” ብለዋል
ሀገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ በወደቀችበት በአሁኑ ወቅት ኢዜማ “ሰላማዊ የትግል ስልቶችን ቀይሶ ታግሎ ማታገል” አለመፈለጉንም አንስተዋል
አቶ አንዱዓለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)ን ከመሰረቱ ፖለቲከኞች ግንባር ቀደሙ ናቸው።
ከፓርቲው ምስረታ በኋላም በምርጫ 2013 ወረዳቸውን በመወከል ተሳትፈዋል፤ የፓርቲው ምክትል መሪ ሆነው እስከማገልገልም ደርሰዋል።
ኢዜማን ለመምራት በተደረገው ፉክክርም ተሳትፎ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
አቶ አንዷለም ዛሬ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ደብዳቤ ከመሰረቱት ፓርቲ መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል፤ ከፓርቲው የለያያቸውን ምክንያቶችም በዝርዝር አስቀምጠዋል።
- ለአዲስ አበባ ከንቲባነት የተወዳደሩት ክቡር ገና ከኢዜማ አባልነት ለቀቁ
- ልዩ ሀይሎች ወደ ፌደራል እና ክልል የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ግልጸኝነት እንዲፈጥር ኢዜማ አሳሰበ
አቶ አንዷለም በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው “…የፓርቲያችንን ቁመናና አሰሳለፍ ከወዲሁ እናስተካክል የሚል ተማጽኖ ከማቅረብም ባለፈ፤ በአባላት ፊት ቀርቤ ብሟገትም የሚገባውን ድጋፍ ባለማግኘቴ ውሳኔያቸውን በጸጋ ተቀብዬ በአባልነት መቀጠሌ ይታወቃል“ ብለዋል።
የቀድሞው የፓርቲው አመራር በኢዜማ “አንኳር በሆኑ ጉዳዮች ላይ በድምጽ ለመሸናነፍ የተደረጉ ፍልሚያዎች” በአዎንታ የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል በደብዳቤያቸው።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከባድ ፈተና ውስጥ ባለችበት ወቅት ፓርቲው ህዝብን የተለያዩ ሰላማዊ የትግል ስልቶችን ቀይሶ ማታገል ሲገባው አፉ መሸበቡንም ነው የጠቆሙት።
“…ገዥዎች ቀልባቸውን እንዲመልሱና ለሁላችንም ድህነት ይሆን ዘንድ መሰራት ቢጠበቅበትም ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆኖ የተሳከረ ሚና በመጫወት እየተንጎላጀ ይገኛል”ም ነው ያሉት።
ፓርቲው ለመሪው ፓርቲ የተለየ ድጋፍ እንደሚያደርግ ባመላከቱበት ጽሁፋቸው፥ “(ፓርቲው) ከስሁት መንገዱ ለመመለስ የማይችልበት መዳፍ ውስጥ” መውደቁንም ያብራራሉ።
“በዕለት ከዕለት ውሎዬ የማገኛቸው ዜጎች አሁንም የፓርቲው አመራር እንደሆንኩ እንደሚቆጥሩ ለመረዳት ችያለሁ” የሚሉት አቶ አንዷለም፥ በፓርቲው የውዳሴም ሆነ ውግዘት ተቋዳሽ መሆን እንደማይፈልጉ በመጥቀስ መልቀቂያቸውን ማስገባታቸውን ጠቅሰዋል።
አደርግኩት ባሉት የሁኔታ ትንተናም የሰነቅነው ህልም እንደማይሳካ ስላረጋገጥኩ “ኢዜማ ውስጥ መቀጠሉ ትርጉም የሚስጥ ሆኖ አላገኘሁትም” አንው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እስካሁን ስለአቶ አንዷለም የመልቀቂያ ደብዳቤና ስለተነሱት ቅሬታዎች የሰጠው ምላሽ የለም።