ብሊንከን በመጪው ሳምንት ኬንያን ጨምሮ በ3 የአፍሪካ ሃገራት ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
ቀጣይዋን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሴኔጋልን ጨምሮ ብሊንከን የሚጎበኟቸው ሃገራት መሪዎች በጠ/ሚ ዐቢይ በዓለ ሲመት መገኘታቸው የሚታወስ ነው
ብሊንከን ኬንያን፣ ናይጄሪያንና እና ሴኔጋልን ይጎበኛሉ ተብሏል
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን በመጪው ሳምንት ኬንያን ጨምሮ በሶስት የአፍሪካ ሃገራት ጉብኝት ሊያደርጉ ነው፡፡
ብሊንከን ከኬንያ በተጨማሪ ናይጄሪያ እና ሴኔጋልን ነው የሚጎበኙት፡፡
ጉብኝቱ በመጪው ሳምንት ሰኞ የሚጀምር ሲሆን ለ6 ቀናት ማለትም እ.ኤ.አ ከህዳር 15 እስከ 20 ይዘልቃል ነው ከመስሪያ ቤታቸው ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ የሚለው፡፡
ጄፍሪ ፌልትማንን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ የሾመችው አሜሪካ አንድ ዓመትን ያስቆጠረው ግጭት እንዲቆምና ወደ ስምምነት እንዲመጣ ግፊት እያደረገች መሆኑ ይታወቃል፡፡
በጠ/ሚ ዐቢይ የሚመራው መንግስት ግጭቱን ለማቆም አልፈቀደም በሚል ምክንያት ኢትዮጵያን ራሷ ካመቻቸችው የንግድ ችሮታ (አጎዋ) ማስወጣቷ ይታወሳል፡፡
ሆኖም ግፊቱ ሚዛናዊ አይደለም ወገንተኝነትም ይታይበታል በሚል መንግስት የዋሽንግተንን እርምጃ መኮነኑ የሚታወስ ነው፡፡
በናይሮቢ ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ራሽል ኦማሞ ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያና በሌሎችም ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
የሶማሊያ እና የሱዳን እንዲሁም ወቅታዊ የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ የምክክሩ መቃኛ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡
ብሊንከን እና ኬንያታ ከአሁን ቀደምም የበይነ መረብ ውይይት አድርገው ነበረ፡፡
በቅርቡ ወደ አሜሪካ ተጉዘው የነበሩት ኬንያታ ግጭቱን ለማስቆም ኢትዮጵያውያን ይወያዩ ሲሉ ከሰሞኑ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡
የናይጄሪያ እና የሴኔጋል መሪዎችን አግኝተው በጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በሌሎች የትብብር ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩም ነው የተነገረው፡፡
የኬንያ፣ የናይጄሪያ እና የሴኔጋል መሪዎች ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም መገባደጃ ላይ ተካሂዶ በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በመሆኑም አሜሪካ ተቀራርባ መስራት ትፈልጋለች፡፡
ብሊንከን በስልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያውን ጉብኝት ነው በአፍሪካ የሚያደርጉት፡፡