የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ፤ ጄፍሪ ፌልትማን ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ ተባለ
ከ10 ቀናት በፊት ሱዳን የነበሩት ፌልትማን ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው
ልዩ መልዕክተኛው ለሁለት ቀናት ጉብኝት ነው ነገ አዲስ አበባ የሚገቡት
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ ተባለ፡፡
ፌልትማን ነገ ሃሙስ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ/ም አዲስ አበባ እንደሚገቡ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ፤ ልዩ መልዕክተኛው ለሁለት ቀናት ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዙ ነው የተናገሩት፡፡
አሜሪካ የጦርነቱን መባባስ በመግለጽ፤ ከፍ ያለ ስጋት እንዳደረባት እና ሁሉም አካላት ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ ስታደርግ ነበር፡፡
ልዩ መልዕክተኛውም ይህንኑ ታሳቢ አድርገው ነገ አዲስ አበባ እንደሚደርሱ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ በጥቅምት 24 2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች ድንገተኛ ጥቃት የተሰዉ የሰሜን ዕዝ የሰራዊት አባላትን አንደኛ ዓመት ዛሬ አስባ ነው የዋለችው፡፡
ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ/ም በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የሚመራ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቆጣጠሩት፣ ለ6 ወራት የሚቆይ እና በመላው ሃገሪቱ የሚተገበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡
ከአሁን ቀደም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩትና ከ10 ቀናት በፊት ሱዳን የነበሩት ፌልትማን ይህንኑ ታሳቢ አድርገው እንደሚመጡም ነው የተነገረው፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል አዲሀገራይ አካባቢ የሚገኘው አዲቡክራይ የህወሓት ማሠልጠኛ ማዕከል በአየር ኃይል ተመቷል ብሏል፡፡
“በማሠልጠኛ ማእከሉ በአሁኑ ወቅት ህወሓት ለሸብር ተልእኮ የተመለመሉ በርካታ ታጣቂዎችን እያሠለጠነበት ይገኛል” ሲልም ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።