ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት የእነ ተመስገንን የዋስትና መብት "አልቀበልም" አለ
የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞች እና በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ እያካሄደ ያለው እስር ትችት አስከትሎበታል
መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የህግ ማስከበር ነው በማለት የቀረበበትን ትችት አይቀበልም
ይግባኝ ሰሚ ችሎት እነ ተመስገን ደሳለኝ በ10 ሺ ብር ዋስትና እንዲወጡ የተወሰነውን ውሳኔ ሻረ።
በዚህም መሠረት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መዓዛ መሐመድና ሰለሞን ሹምዬ ለተጨማሪ 8 ቀን በእስር እንዲቆዩ ተወስኗል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ የሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም ፖሊስ ለፌደራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ነበር።
ይግባኙን የተመለከው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ፤ በታችኛው ፍ/ቤት የተሰጠውን የዋስትና መብት በመሻር፣ የፖሊስን ይግባኝ ተቀብሏል።
በዚህም መሠረት ሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በእስር እንዲቆዩና ፖሊስ ምርመራውን እንዲቀጥል ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት ለፖሊስ ተጨማሪ 8 ቀናትን በመስጠት ፤ የታችኛው ፍ/ቤት ውሳኔ ከሰጠበት ቀን ጀምሮ የሚቆጠር ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል። ይህም በመሆኑ ለሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል ።
የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞች እና በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ እያካሄደ ያለው እስር ትችት አስከትሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ)ም የመንግስት የእስር ድርጊት ኮንኗል፡፡
ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት ተችዎችን እያሰራ አለመሆኑን እና እየሰራ ያለው ስራ የህግ የማስከበር ተግባር መሆኑን በተጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል፡፡