ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ግንቦት 18 ነበር ከስራ ቦታ በጸጥታ ኃይሎች የተያዘው
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ሰለሞን ሹምየ እያንዳንዳቸው በ10ሺ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡
የፍትሕ መጽሔት ማኔጅንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ተመስገን"ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በዩቱብ ኢንተርቪዎችን በመስጠት ቀስቅሷል" በሚል ነበር በፖሊስ ተጠርጥሮ የታሰረው፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መንግስት ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት በተደጋጋሚ ሲታሰር ሲፈታ ቆይቷል፡፡
ከእስር ከተፈታ በኋላ በድጋሚ ወደ ሚዲያ ስራ ተመልሷል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የተያዘው ከስራ ቦታ መሆኑን ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ እና የስራ ባልደረቦቹ ገልጸው ነበር፡፡
ገበያኑ በተባለ ሚዲያ በግሉ ሲሰራ የነበረው ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምየም በዛሬው እለት በአራዳ ምድብ ችሎት የቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ በ10ሺብር ዋስ እንዲፈታ ወስኗል፡፡ ቀደም ሲል በእስር ላይ ነበረችው ጋዜጠኛ መአዛ መሃመድም በዋስ እንድትለቀቅ ተወስኖላታል፡፡
ከጋዜጠኛ ተመስገንና እና ሰለሞን ሹምየ ጋር ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ እና መስከረም አበራ ተጨማሪ የስድስት ቀን የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞች እና በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ እያካሄደ ያለው እስር ትችት አስከትሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ)ም የመንግስት የእስር ድርጊት ኮንኗል፡፡
ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት ተችዎችን እያሰራ አለመሆኑን እና እየሰራ ያለው ስራ የህግ የማስከበር ተግባር መሆኑን በተጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል፡፡