አሜሪካ በሩሲያ ጉዳይ ቻይናን አስጠነቀቀች
አሜሪካ ቻይናን ጨምሮ ለሩሲያ ማንኛውንም ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሀገራትን በቅርበት እየተከታተለች ነው ብላለች
ቻይና ለሩሲያ ድጋፍ ካደረገች “ዋጋ ትከፍላለች” ስትል አሜሪካ ዝታለች
አሜሪካ በዩክሬን ጉዳይ ቻይና ለሩሲየ ድጋፍ እንዳታደርግ አስጠንቅቃለች።
ቤጂንግ ለሞስኮ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ካቀረበች “ዋጋ ትከፍላለች” ስትል አሜሪካ መዛቷንም ተሰምቷል።
የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኮሚሽን ዳይሬክተር ጋር በትናትናው እለት በጣሊያን ሮም ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የአሜሪካው ልኡክ ዋሽንግት ያላትን ስጋት ለቻይና ግልጽ ማድረጋቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ አስታውቀዋል።
ኔድ ፕራይስ በመግለጫቸው አክለውም፤ አሜሪካ ቻይናን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኝ ለሩሲያ የቁስቁስ፣ የገንዝብ፣ የሃሳብ እና ማንኛውንም ድጋፍ የሚያደርጉ ሀገራትን በቅርበት እየተከታተለች ነው” ብለዋል።
“በግልም ይሁን በይፋ አሜሪካ ያላትን አቋም ለቤጂንግ ይፋ አድርጋለች” ያሉት ቃል አቀባዩ “ቻይና ከዚህ በማለፍ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ለሞስኮ ካቀረበች ዋጋ ያስከፍላታል” ሲሉም ዛቻ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል።
ቻይና፤ ሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ እንደጠየቀቻት ተደርጎ ከሰሞኑ ሲሰራጭ የነበረው ዜና ሀሰት መሆኑን በትናትናው እለት ማስታወቋ ይታወሳል።
ሩሲያ፤ ቻይና ወታደራዊ ድጋፍ እንዲታደርግላት መጠየቋን ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግረው እንደነበር ተዘግቧል።
ለጉዳዩ ሽፋን ከሰጡት መካከል ፋይናንሻል ታይምስ፣ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ሲኤንኤን፣ እንዲሁም ሌሎች ሚዲያዎች ሩሲያ፤ ሩሲያ ቻይና የድሮን ድጋፍ እንድታደርግላት ጠይቃለች በሚል ዘገባዎችን ሲያሰራጩ ነበር።
በአሜሪካ ያለው የቻይና ኤምባሲ ሞስኮ እና ቤጂንግን በተመለከተ የተሰራጨው ዜና ሙሉ በሙሉ ሃሰት መሆኑን ይፋ አድርጓል።