የአውሮፓ የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነር ዛሬ ወደ ሱዳን አቅንተው ተፈናቃዮችን ይጎበኛሉ
ህብረቱ የገንዘብ ድጋፎችን ጭምር በማቋረጥ በኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደር ውጥን አለው
“ኢትዮጵያ ለገንዘብ ስትል ልትለውጥ የምትችለው ሉዓላዊነት የላትም”- ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ
ያኔዝ ሊናርቺች ዛሬ ወደ ሱዳን አቅንተው ተፈናቃዮችን ይጎበኛሉ
ከሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር መወያየታቸውን የገለጹት የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነር ያኔዝ ሊናርቺች ዛሬ ወደ ሱዳን ያቀናሉ፡፡
ኮሚሽነሩ ከሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሚወያዩ ሲሆን ከውይይቱ በኋላ በከሰላ እና ገዳሪፍ ግዛቶች የተጠለሉ የኢትዮጵያ ተፈናቃዮችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል፡፡
በተፈናቃዮቹ ዙሪያ ከወ/ሮ ሙፈሪያት የተወያዩት ሊናርቺች ኢትዮጵያ በግጭቱ ወደ ተጎዱ አካባቢዎች መድረስ የሚፈልጉ የእርዳታ ሰራተኞችን መተባበር እንዳለባት እና የህብረቱ አባል ሃገራት ዜጎች ከግጭቱ አካባቢ የሚወጡበትን ሁኔታ እንድትፈቅድ ማሳሰባቸውን አል ዐይን አማርኛ ቀደም ሲል ዘግቧል፡፡
ህብረቱ የገንዘብ ድጋፎችን ጭምር በማቋረጥ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደር ውጥን አለው እንደ ሰሞነኛው የፖለቲኮ መጽሄት ዘገባ፡፡
ሆኖም ከትናንት በስቲያ ሰኞ በልዩ ሁኔታ ለተሰበሰበው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለገንዘብ ስትል ልትለውጥ የምትችለው ሉዓላዊነት እንደሌላት መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
ህብረቱ ወደ አውሮፓ በሚያቀኑ ህገ ወጥ ስደተኞች የሚታመስ ነው፡፡ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር በመቀናጀት ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚያቀኑ ህገ ወጥ ስደተኞችን ጉዳይ ለማስታመም ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ለአንድ ሚሊዬን የቀረቡ ስደተኞችን ተቀብላ ከምታስተናግደው ኢትዮጵያ እና ከሌሎችም የአፍሪካ ሃገራት ጋር ተቀራርቦ ይሰራል፡፡
ባለፉት 8 ዓመታት ለኢትዮጵያ ብቻ የ815 ሚሊዬን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በአፍሪካ ትረስት ፈንድ በኩልም የ400 ሚሊዬን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ሆኖም በኢትዮጵያ መንግስት የተጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ እምብዛም የተዋጠለት አይመስልም፡፡
ምናልባትም ግጭቱ ቀጣናዊ መልክ ይዞ ዳግም በስደተኞች ልጥለቀለቅ እችላለሁ በሚል ስጋት ከአሁን በኋላ ጉዳዩን በህግ ማስከበር ስም ለመመልከት እንደሚቸገር ከሰሞኑ በብራሰልስ ጉብኝት ላደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ማስታወቁን ነው በፖለቲኮ የሰፈሩ መረጃዎች ያመለከቱት፡፡