በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ለመርዳት 49.7 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል- ተመድ
ገንዘቡ መሰረታዊ የምግብ ፍጆታዎች፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን ይውላል
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት 49 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በወራዊ ሪፖርቱ ላይ እንዳስታወቀዉ ገንዘቡ መሰረታዊ የሆኑ የምግብ ፍላጎቶችን ለማሟላት እንዲሁም ለተፈናቃዮቹ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያስችል ነው ብሏል።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በትግራይ ክልል ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ አስከ ሰኔ 2021 ድረስ የሚስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ድጋፍ መጠየቁንም አስታውቋል።
ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን መንግስት ዋቢ በማድረግ ባወጣው መረጃ በትግራይ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፤ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ ሀገሪቱ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከ800 ሺህ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች ትገኛለች።
አብዛኞች ስደተኞችም ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን እና ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ መሆናቸውንም በተባሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።