“በሸኔ ታጣቂዎች ተከበናል መንግስት ይድረስልን”-የድባጤ ወረዳ ተፈናቃዮች
“ትናንት እና ከትናንት ወዲያ በተፈጸመብን ጥቃት ቀያችን ለቀን ወጥተናል”-ከተፈናቃዮቹ መካከል
“ሁኔታዎችን እንዲያጣራ ወደ አካባቢው የላክነው ቡድን በሚያገኘው መረጃ መሰረት እርምጃ እንወስዳለን”-የዞኑ የኮማንድ ፖስት
“በሸኔ ታጣቂዎች ተከበናል መንግስት ይድረስልን”-የድባጤ ወረዳ ተፈናቃዮች
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከድባጤ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው ጋሊሳ ከተባለ የወረዳው ቀበሌ ሰፍረው የሚገኙ “የአማራ ተወላጅ ነን”ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ጥሪ አቀረቡ፡፡
“ትናንት እና ከትናንት ወዲያ በተፈጸመብን ጥቃት ቀያችን ለቀን ወጥተናል”ያሉት ነዋሪዎቹ “አሁንም ባረፍንበት ቀበሌ የኦነግ/ ሸኔ ታጣቂዎች እየተመላለሱ እያስፈራሩን ነው” ብለዋል፡፡
አንድ ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ እና ከተፈናቃዮቹ መካከል የሆኑ ግለሰብ “ጨለማን ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱ የሸኔ ተጣቂዎች አሉ ሌሊቱን በእነሱ ተከበን ነው ያደርነው” ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ግለሰቡ “ነዋሪው ተፈናቅሎ ጋሊሳ ላይ በየጎዳናው ፈስሶ ይገኛል ነው”የሚሉት፡፡
ቁጥሩን “በትክክል ለመናገር እቸገራለሁ”ቢሉም ከ5 እስከ 6 ሺ ሊደርስ እንደሚችል ይገምታሉ፡፡
“እንዲህ የሆንነው ለነዋሪው ጠበቃ መሆን ሲገባው ወደ እኛው በሚተኩሰው የክልሉ ልዩ ኃይል ጭምር ነው” የሚሉት ግለሰቡ “አብረው ነው የሚሰሩት፤ ተማምለዋል ሲባልም እንሰማለን፤ ትዕዛዝ የሚሰጣቸውም አካል አለ”ሲሉ ያክላሉ በተናበበ መንገድ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ለመጠቆም፡፡
“ባለንበት መጥተው እስከሚጨርሱን ነወይ የሚጠበቀው በአስቸኳይ ይድረስልን” ሲሉም ለመንግስት ጥሪ ያቀርባሉ፡፡
በዞኑ በሃገር መከላከያ ሰራዊቱ እና በፌዴራል ፖሊስ በሌሎች አጋር አካላት ጭምር የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ እና እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንኳን ከሰሞኑ በወረዳው (ድባጤ) በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ባደረሱ እና “ፀረ-ሠላም” ባላቸው ኃይሎች ላይ በተወሰደው እርምጃ ከ20 በላይ የሚሆኑ ኃይሎች ስለመደምሰሳቸው አስታውቋል።
ከሰሞኑ መነሻውን ቡለን ወረዳ ዶቢ ቀበሌ አድርጎ ወደ ወረዳው ሲንቀሳቀስ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ቂዶህ ቀበሌ ላይ ሲደርስ በተሳፋሪዎቹ ላይ በተፈጸመው ጥቃት በርካቶች ተገድለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሟቾቹን ቁጥር 34 ያደርሰዋል፤ ቁጥሩ ከዚህም ሊያሻቅብ እንደሚችል በማስቀመጥ፡፡
ይህን የኮማንድ ፖስቱን እንቅስቃሴ በማስታወስ በአካባቢያቸው የሚንቀሳቀስ ሰራዊት እያለ እንዴት ሊጠቁ እና ሰራዊቱስ እንዴት ሊደርስላቸው እንዳልቻለም አል ዐይን አማርኛ ጠይቋል፡፡
“እኛ አካባቢ አንድም የመከላከያ ኃይል የለም፤ ቀደም ሲል የነበረው ከወጣም ከ15 ቀናት በላይ አልፎታል” ሲሉ የሚመልሱት ግለሰቡም “መከላከያው ያድናችሁ እንደሆነ እናያለን፤ ሲወጣ የት እንደምትገቡም እንተያያለን በሚል ሲያስፈራሩን ነበር”ም ብለዋል፡፡
“ዛሬን እንኳ ማደራችንን እርግጠኛ አይደለንምና እባካችሁ ለመንግስት አሳውቁልን” ሲሉም ነው ግለሰቡ የሚማጸኑት፡፡
አል ዐይን አማርኛም የዞኑን የኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል አያሌው በየነን በስልክ ስለ ጉዳዩ ጠይቋል፡፡
“አካባቢው ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለበት ኔትወርክም የማይሰራበት ነው” ያሉት ሰብሳቢው “ስለተባለው ነገር ያወቅነው ነገር የለም” ብለዋል፡፡
የተባለው ሁሉ እውነት ላይሆን እንደሚችል እና ከስጋት ውጪ በአካባቢው የደረሰ ጥቃት እንደሌለ ካለም ለጸጥታ ኃይሉ እንደሚያሳውቁ ነው የተናገሩት፡፡
ችግሮች በነበሩበት አልባሳ አካባቢ ከ3 ቀናት በፊት የጸጥታ አካል ልከናል ብለዋል፡፡
አሁንም ወደ ጋሊሳ “ሁኔታዎችን እንዲያጣራ” የተላከ ቡድን እንዳለም ነው የገለጹት፡፡
ቡድኑ የሚያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም አስታውቀዋል፡፡