በዞኑ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ከስፍራው የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ
በዎላይታ ዞን በተፈጠረው አለመረጋጋት የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ
በትናንትናው ዕለት የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እና አክቲቪስቶችን ጨምሮ 26 ሰዎች መታሰራቸውን ተከትሎ በዞኑ በተለይም በሶዶ ከተማ በተከሰተው ሁከት በትንሹ የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን አል ዐይን ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አንድ የዞኑ ባለስልጣን ለአል ዐይን በስልክ እንዳረጋገጡት በሶዶ ከተማ ትናንት ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ሰልፈኞ ላይ በፀጥታ ሀይሎች በተወሰደ እርምጃ የ4 ሰዎች ህይወት አልፏል። በዛሬው ዕለትም የ2 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ተናግረዋል። በቦዲቲ ከተማም እንዲሁ 4 ሰዎች መገደላቸውን እንዳረጋገጡ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ባለስልጣን ተናግረዋል። የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ነው የገለፁት።
ከሞቱት በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውንም ገልፀዋል።
በደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በተሰጠ መግለጫ በተፈጠረው ሁከት 5 ሰዎች ብቻ እንደተገደሉ ነው የተገለፀው።
በዛሬው ዕለትም የተለያዩ አመራሮች እና ሌሎች ተፈላጊ ግለሰቦች እየታደኑ በመያዝ ላይ እንደሚኙ አል ዐይን ከምንጮቹ አረጋግጧል።
በዞኑ የተለያዩ ከተሞች የተነሳው ሁከት ዛሬ ከሰዓት ላይ የመረጋጋት ባህሪ በማሳየት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በሶዶ ከተማ እና ሌሎች ሁከት የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ጎዳና ወጥተው ከፖሊስ ጋር የተጋጩት ሰልፈኞች አሁን ላይ ወደ ቤታቸው ስለመመለሳቸው ከተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው የዐይን እማኞች ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ ወደ ዎላይታ ዞን መግባትም ሆነ መውጣት እንደማይቻል አስተያየታቸውን የሰጡን እማኞች ፣ በዞኑ ምንም እንቅስቃሴ እንደሌለ ተናግረዋል። በሶዶ ከተማ አሁንም አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጾች እንደሚሰሙም የደረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከ2 ሳምንታት በፊት በስም የተለዩ ግለሰቦችን ቤትና ንብረት ለማቃጠል እና ለማውደም የታቀደ እንቅስቃሴ እንደነበር አል ዐይን ያነጋገራቸው ግለሰቦች የገለጹ ሲሆን ድርጊቱ ሊፈጸም ከተያዘለት ጊዜ ከሰዓታት በፊት ለመንግሥት ጥቆማ በመሰጠቱ የጸጥታ አካላት በመግባታቸው ዕቅዱ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል። ትናንት ተፈጥሮ እስከ አሁን በዘለቀው ሁከት ብሔር ተኮር ጥቃት እና ንብረት የማቃጠል ድርጊት እንዳይፈጸም ወጣቶች ተደራጅተው ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር ምንጮቻችን ገልፀዋል።
የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በተመለከተ ትናንት መግለጫ የሰጠው የደቡብ የክል መንግስት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ፣ አመራሮቹ በአካባቢው ግጭት ለመቀስቀስ በተደራጀ መንገድ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውቋል።
በምክትል ር/መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አለማየሁ ባውዲ እንዳሉት የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የተለያዩ ህገወጥ አደረጃጀቶችን ፈጥረው ግጭት የመቀስቀስ ፍላጎታቸውን እንዲያስፈጽሙ እያደረጉ ነበር። በፓርቲም በግለሰብም ደረጃ ሀገር ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ በማለት አቶ አለማየሁ ከገለጿቸው የህወኃት እና የኦነግ ሸኔ አካላት ጋር በድብቅ ሰው እየላኩ ስብሰባ እንደሚያደርጉ እና ተልዕኮ እንደሚቀበሉም በመግለጫቸው ይፋ አድርገዋል። ለዚህም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት መረጃዎች ተገኝተዋል ነው ያሉት አቶ አለማየሁ።
የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ በመተላለፍ ህገወጥ ስብሰባዎችንና ሰልፎችን ማድረጋቸውም ተገልጿል። ህብረተሰቡ የሰጡትን አመራር ቢቀበላቸው በአካባቢው ግጭቶች ይፈጠሩ እንደነበር አቶ አለማየሁ ተናግረዋል። ከህገ መንግሥት ውጭ በመንቀሳቀስ ክልሉን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን በመግለፅ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም በእኩይ ድርጊታቸው መቀጠሉን መምረጣቸውንም አቶ አለማየሁ አብራርተዋል።
የዞኑ አመራሮች ከክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከፌዴራል እና ከደቡብ ክልል መንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል። የዞኑ ክልል የመሆን ጥያቄ በደቡብ ክልል መንግስት ተገቢው ምላሽ አልተሰጠውም በሚል ተቃውሞ በክልሉ ምክር ቤት የዞኑ ተወካዮች ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ካገለሉ ከ6 በላይ ሳምንታት ተቆጥረዋል። የዞኑ ተወካዮች ወደ ም/ቤት እንዲመለሱ በክልሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ እስካሁን አልተቀበሉም። የዎላይታ ዞን ምክር ቤት በራሱ ጊዜ ዞኑን በክልል ለማደራጀት ወስኖ ይህን ስራ የሚያስፈጽም ምክር ቤት ማቋቋሙ ይታወሳል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደቡብ ክልል የዞንና የወረዳ አመራሮችን ሰብስበው ከአደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የክልሉን ህዝብ ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲያስቆሙ አሳስበዋል። የዞንና የወረዳ የፖለቲካ ስራዎች በአክቲቪስቶች መጠለፋቸውንም በመግለፅ አመራሩ ከጽንፈኛ እና ህገወጥ አካሄድ ካልተመለሰ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል። የክልል ጥያቄዎች የጸብ ምንጭ መሆን እንደሌለባቸው እና ጥያቄዎቹ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ምላሽ እንደሚያገኙ ስምምነት መደረሱንም አስታውሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጥረት የነገሰባቸውን የዎላይታ ፣ የጋሞ እና የጎፋ ዞን አመራሮችን ከቀናት በፊት በተናጥል ማወያየታቸውም ይታወቃል።