የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ቭላድሚር ፑቲንን ለማግኘት ወደ ሩሲያ ተጓዙ
ዩክሬን ወደቦች ላይ በቀሩ የምግብ እና የማዳበሪያ ጉዳዮች ላይ ፑቲንን ያወራሉ ተብሏል
ማኪ ሳል በሶቺ ፕሬዝዳንት ፑቲንን እንደሚያገኙ ይጠበቃል
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ነገ አርብ በሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ያነጋግራሉ ተባለ፡፡
ማኪ ሳል በጦርነቱ ምክንያት ዩክሬን ወደቦች ላይ በቀሩ የምግብ እና የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ግብዓቶች ጉዳይ ላይ ለማውራት ነው ፑቲንን የሚያገኙት፡፡
በሪዞርት ከተማዋ ሶቺ እንደሚገናኙም፤ ማኪ ሳል በፕሬዝዳንት ፑቲን ግብዣ ወደ ሩሲያ ማቅናታቸውን ያስታወቀው ጽህፈት ቤታቸው ገልጿል፡፡
ከሩሲያ መልስ ወደ ጋና አክራ አቅንተው በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ጉባዔ ላይ እንደሚገኙም ነው ጽህፈት ቤቱ የገለጸው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል ቭላድሚር ፑቲንን አደነቁ
ኢኮዋስ በመጪው ቅዳሜ በማሊ፣ በጊኒ እና በቡርኪና ፋሶ የመፈንቅለ መንግስት ጉዳዮች ላይ ይመክራል፡፡
ሊቀመንበሩ ከፑቲን ጋር በሚገናኙበት ወቅት በጥቁር ባህርና በሌሎችም የዩክሬን ወደቦች የሚገኙት ምርቶቹ ወደ አፍሪካ ሊገቡ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
ጦርነቱ ሊረግብና ሰላማዊ መላዎች ሊዘየዱ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉም ነው ዘገባዎች ያሉት፡፡
ቭላድሚር ፑቲን፤ የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት መልዕክት ላኩ
ማኪ ሳል ከህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ነው ወደ ሩሲያ ያቀኑት፡፡ ዛሬ ሃሙስ ሞስኮ እንደሚደርሱ የሚጠበቅ ሲሆን ነገ አርብ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን አግኝተው ያነጋግራሉ ተብሏል፡፡
የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ትናንት ረቡዕም ከአውሮፓ ህብረት የምክር ቤት አባላት ጋር የበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል፡፡ ስለ ዩክሬን ጦርነትና ጦርነቱን ተከትሎ ስላጋጠመው የምግብ አቅርቦት ችግር ተወያይተዋል፡፡
ሩሲያ በመላው ዓለም ያጋጠመው የምግብ አቅርቦት ችግር ከጦርነቱ ጋር ከወሰደቻቸው እርምጃዎች ይልቅ በምዕራባውያኑ ማዕቀብ ምክንያት የመጣ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሆኖም የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑዔል ማክሮን ሩሲያ ጉዳዩን በመያዣነት እንደወጥመድ እየተጠቀመችበት ነው በሚል ወቅሰዋል፡፡
ማኪ ሳልም አውሮፓ እና አፍሪካ እንደመያዣ መጠቀሚያ ሊሆኑ አይገባም የሚለውን የማክሮንን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ይህንንም ትናንት ከህብረቱ ተወካዮች ጋር በነበራቸው ስብሰባ አንጸባርቀዋል፡፡
የሩሲያ መንግስት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ስለ ጉዳዩ ያለው ነገር የለም፡፡