ሚኒስትሮቹ ነገ ሃሙስ በቱርክ አንታሊያ ከተማ ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሏል
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር በአካል ሊገናኙ መሆኑን ተገለጸ፡፡
የሁለቱ ሀገራት ሚኒስትሮች ነገ በቱርኳ አንታልያ ከተማ እንደሚገናኙ የሃገራቱ መንግስታት አስታውቀዋል፡፡ ሁለቱ ሚኒስትሮች ነገ በአካል ሲገናኙ ጦርነት ውስጥ ከገቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው፡፡
ኪቭ እና ሞስኮ ወደ ጦርነት ካመሩ ወዲህ በባለስልጣኖቻቸው በኩል የፊት ለፊት ንግግር ቢጀምሩም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻው በኩል ግን የነገው ግንኙነታቸው የመጀመሪያ ነው፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ላቭሮቭ ከዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር እንደሚገናኙ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአካል መገናኘት ሁኔታውን ወደ ሰላምና መረጋጋት ሊወስደው እንደሚችል ገምተዋል፡፡
ሁለቱ ሚኒስትሮች በደቡብ ቱርክ በምትገኘው የሪሶርት ከተማ አንታልያ የሚገናኙት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶሃን ባደረጉት ጥረትና ሀገራቸው በሰራችው ዲፕሎማሲያዊ ስራ መሆኑንም ካቩሶግሉ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
የዩክሬኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩሌባ ለንግግር ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልጹም ይህ የሚሆነው ግን ንግግሩ ውጤታማ ከሆነ ነው ብለዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቱርኩ አቻቸው ረጂብ ጣኢብ ኤርዶህን በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር ለመገናኘት መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡
የሩሲያ እና የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሶስተኛ ዙር ንግግር እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከዩክሬን መፈናቀላቸው ተነግሯል፡፡