ፕሬዝዳንት ባይደን የሩሲያ ኢኮኖሚ የደም ስር ነው ባሉት ነዳጅ ላይ እገዳ መጣላቸውን አስታውቀዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሩሲያ ነዳጅ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ አገዱ፡፡
ባይደን የሩሲያ ኢኮኖሚ የደም ስር ነው ባሉት ነዳጅ ላይ እገዳ መጣላቸውን ትናንት ከቤተ መንግስታቸው ሆነው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በባይደን ውሳኔ መሰረት ከአሁን ቀደም የተደረጉ የነዳጅ ግብይት ስምምነቶች በ45 ቀናት ውስጥ መቋጫ የሚያገኙ ይሆናልም ተብሏል፡፡
እርምጃው ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የተወሰደ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጋለች በሚል ለተከሰሰችው ሩሲያ የተሰጠ ምላሽ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡
ይህ የባይደን እርምጃም የነዳጅ ዋጋን ይበልጥ እንዳያንረው ተሰግቷል፡፡ አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በዓለም ገበያ ከ140 ዶላር በላይ በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡
ሆኖም ፕሬዝዳንቱ እርምጃውን ተከትሎ የሚመጡ ተያያዥ የዋጋ ንረት ችግሮች ቢኖሩም ንረቱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አፋጣኝ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡
እርምጃው ከአውሮፓ አጋሮቻቸው ጋር በመመካከር የተወሰደ መሆኑንም ነው ባይደን የገለጹት፡፡ እንግሊዝን መሰል የአውሮፓ ሃገራት ተመሳሳይ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚችሉ ሲያሳስቡ ነበር፡፡ ሆኖም በሩሲያ የነዳጅ ምርቶች ላይ የከበደ ጥገኝነት ያለባት ጀርመን ሌሎቹን ተከትላ እርምጃ ልትወስድ እንደማትችል አስታውቃለች፡፡ ምክንያቱም ከአሁን ቀደም ኖርድ ስትሪም 2 ተብሎ በሚጠራው የሩሲያ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ላይ በጣለችው እገዳ ምክንያት ለከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ግሽበት ተጋልጣለች፡፡ ይህ አብዛኛው የኃይል ፍጆታዋ በሩሲያ ለሚሸፈነው ጀርመን አደገኛ ነው፡፡
ሃንጋሪና ቱርክም የአሜሪካንና ምዕራባውያንም እናደርገዋለን የሚሉትን ይህን እርምጃ ተቃውመዋል፡፡ የሩሲያን ነዳጅ መግዛታቸውን እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት፡፡ ሃንጋሪ 90 በመቶ የነዳጅ ፍጆታዋን የምታገኘው ከሩሲያ ነው፡፡ ቱርክም ብትሆን 45 በመቶ የተፈጥሮ ጋዝ፣ 17 በመቶ የጋዝ እና 40 በመቶ የቤንዚን ፍላጎቷን ከሩሲያ ነው የምታገኘው፡፡ በመሆኑም መግዛቷን እንደምትቀጥል አስታውቃለች፡፡
እርምጃው አደገኛ እንደሚሆን ያሳሰበችው ሩሲያም የተለያዩ የአጸፋ ምላሾችን ልትሰጥ እንደምትችል አስታውቃለች፡፡ በአሜሪካ የተጣለውን እገዳ ለመቋቋም የሚያስችሉ ጡረታን ከፍ የማድረግና ለአነስተኛና መካከለኛ ቢዝነስ አንቀሳቃሾች መጠነኛ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ውሳኔ መስጠታቸውንም ፕሬዝዳንት ፑቲን ይፋ አድርገዋል፡፡