ምዕራባውያን የሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ከጣሉ በዓለም ገበያ ላይ ያልተጠበቀ አደጋ ያስከትላል ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች
የአውሮፓ ሀገራት 40 በመቶ የተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታቸውን ከሩሲያ ነው የሚያገኙት
በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ከተጣለ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ እስከ 300 ዶላር ሊደርስ ይችላል ብላለች
ሩሲያ ምዕራባውያን የነዳጅ ምርቷ ላይ ማዕቀብ የሚጥሉ ከሆኑ ያልተጠበቀ አደጋ ሊስከትል ይችላል ስትል አስጠነቀቀች።
አንድ የሩሲያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን እንዳስታወቁት ምዕራባውያን የሩሲያ የነዳጅ ምርት ወደ ሀገራቸው እንዳይገባ ክልከላ ከጣሉ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አኤክሳንደር ኖቫክ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፤ የሩሲያ የነዳጅ ምርት ላይ የሚጣል ማንኛውም እቀባ በዓለም ገበያ ላይ አደገኛ የሆነ ችግር ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።
የሩሲያ የነዳጅ ምርት ላይ እቀባ ከተጣለ አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ እስከ 300 የአሜሪካ ዶላር ሊደርስ እንደሚችልም አስታውቀዋል።
ከዚህ በዘለለም ሩሲያ ለአውሮፓ የተፈጠሮ ጋዝ የምታቀርብበትን ኖርድ ስትሪም ማስተላለፊያ እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችልም አሳስበዋል።
የሩሲያ ማስጠንቀቂያ የመጣው አሜሪካ እና የአውሮፓ አጋሮቿ የሩሲያ ነዳጅ እና የጋዝ ምርት ወደ ሀገራቸወ እንዳይገባ በመከልከል ሩሲያን ለመቅጣት አስበዋል መባሉን ተከትሎ ነው።
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አኤክሳንደር ኖቫክ፤ የአውሮፓ ሀገራት የሩሲያ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መቀበል ካቆሙ፤ ከሩሲያ የሚያገኙትን የነዳጅ ምርት ለመተካት ዓመታትን ሊፈጅባቸው ይችላል ብለዋል።
በተጨማሪም ከሩሲያ ነዳጅ መቀበል በሚያቆሙበት ጊዜ ምን ሊያስከትል እንደሚችል የአውሮፓ ፖለቲከኞች ለዜጎቻቸው በግልጽ ማሳወቅ አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።
“ከሩሲያ የነዳጅ እና ሌሎቸ የኃይል አማራጮችን መቀበል ማቆም ከፈለጋችሁ መቀጠል ትችላላችሁ” ያሉት ምክትል ጠቅላ ሚኒስትሩ፤ “ምርቶቻችንን ወዴት ማዞር እንደዳለብን ጠንቅቀን እናውቃለን” ብለዋል።
ሩሲያ 40 የአውሮፓ የጋዝ አቅርቦትን የምትሸፍን ሲሆን፤ በዓለም ላይ ግንባር ቀደም ከሆኑ የነዳጅ አቅራቢ ከሆኑ ሀገራትም አንዷ ነች።
ሩሲያ በቀን 7 ሚሊየን ድፍድፍ ነዳጅ ለዓለም ገበያ ታቀርባለች የተባለ ሲሆን፤ ይህም የዓለም አቀፍ አቅርቦት ውስጥ 7 በመቶውን ይሸፈፍናል።