የአፍሪካ ህብረት፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዱትን እርምጃ አደነቀ
ህወሓት ከቀናት በፊት ባሰራጨው ደብዳቤ በኦባሳንጆን አደራዳሪነት ላይ ጥያቄ እንዳለው ማንሳቱ አይዘነጋም
ሙሳ ፋኪ ኦባሳንጆን ስላደረጉት ጥረት አመስግነዋል
የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዱትን እርምጃ አደነቀ፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ግጭቱን ለማርገብና ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሄዱበትን ርቀትና ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት፣ በትግራይ በኩል የጦር ምርኮኞቹ በከፊል እንዲለቀቁ መደረጉ፣ ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ፣ ለሰብአዊነት ሲባል ተኩስ እንዲቆም መደረጉ እና የትግራይ ኃይሎች ከተቆጣጠሯቸው የአፋር አካባቢዎች መውጣታቸው” መተማመን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉልህ እርምጃዎች እንደነበሩም ገልጸዋል ሊቀ መንበሩ፡፡
ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ለሰብአዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉን ተከትሎ ለተጎዱ ክልሎች የሰብአዊ አቅርቦትና ድጋፍ በማቅረብ ረገድ የሚታዩ መሻሻሎችን ህብረቱ በጸጋ የሚቀበላቸው ናቸውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና ህወሓት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዷቸውን እርምጃዎችም አድንቀዋል፡፡
ህብረቱ የተጀመሩ ፖለቲካዊ ውይይቶች መቀጠላቸውን እንደሚያበረታታም ጭምር ነው የገለጹት፡፡
ሊቀ መንበሩ ይህን ያሉት፤ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ አድርገው የሾሟቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡
በንግግሩ ኦባሳንጆ “የተሰጣቸውን ተልእኮ አፈጸጸም” በተመለከተ ለሊቀ መንበሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
“የኢትዮጵያን ችግር በድርድር ለመፍታት” እያደረጉት ስላለው ያላሰለሰ ጥረትም ሙሳ ፋኪ ማሃማት ኦባሳንጆን አመስግነዋል፡፡
ለተገኙ ውጤቶች የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካዩ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከፍተኛ ነበርም ነው ሙሳ ፋኪ ያሉት፤ አሁንም የተሻለ ተሳትፎ በማድረግና አጠቃላይ ግጭቶችን በማቀዝቀዝ ግጭት የማርገቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመጠቆም።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በህብረቱ መሪነት በመደረግ ላይ ያሉ የሰላም ጥረቶችን እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሙሳ ፋኪ ስለ ኦባሳንጆ የአፈጻጸም ውጤት ይህን ይበሉ እንጂ፤ ህወሓት ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በኦባሳንጆ አደራዳሪነት ላይ ጥያቄ እንዳለው ማንሳቱ አይዘነጋም፡፡
ህወሓት ለተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት በጻፈውና የድርጅቱ ሊቀ መንበር ፊርማ ባረፈበት ደብዳቤው “ኦባሳንጆ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያላቸው ቅርበት የትግራይ ህዝብ ሳያስተውለው ቀርቶ አይደለም” በማለት በኦባሳንጆ አዳራደሪነት ያለው እምነት እምብዛም እንዳልሆነ መግለጹ ይታወሳል፡፡