የአፍሪካ ህብረት ተወካዩ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ መቀሌ እንደነበሩ የህወሓት ቃል አቀባይ አስታውቀዋል
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ መቀሌ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡
ቃል አቀባዩ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ኦባሳንጆን ተቀብለው ማነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡
“በቀጠናዊ ጉዳዮች” ላይ መምከራቸውንም ገልጸዋል ቃል አቀባዩ፡፡ ሆኖም ”ቀጣናዊ” የተባለው ጉዳይ ምን እንደሆነ አቶ ጌታቸው በግልጽ አላስቀመጡም፡፡ የተወያዩባቸው ተጨማሪ ጉዳዮች እንዳሉም አልገለጹም፡፡
የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት የመቀሌ ጉዞ በተመለከተ የፌዴራል መንግስቱ የሰጠው መግለጫም ሆነ ያለው ነገር የለም፡፡
ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የፌዴራል መንግስቱንና ህወሓትን በማቀራረብ ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ኃላፊነት መሰጠታቸው ከተነገረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
ኃላፊነታቸውን ከዳር ለማድረስ እንደሚያስችሉ የታመነባቸውን ተደጋጋሚ ጉዞዎችንም ወደ መቀሌ እና አዲስ አበባ አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)ም ከሰሞኑ ናይጄሪያን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡
መሪው ፓርቲ ብልጽግና ከህወሓት ጋር ያለውን ችግር በየትኛውም የሰላም አማራጭ ለመፍታት መስማማቱን ከአሁን ቀደም ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ህወሓት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ እንደሆነ መገለጹ በሰላም ጥረቱ ላይ ጥላ እንዳያጠላ የብዙዎች ስጋት ነው፡፡