በኢትዮጵያ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል- ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ
በኢትዮጵያ ጉዳይ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማበጀት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል
በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ከሰሞኑ በሰሜን ኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል
የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ላለው የሰብአዊ ሁኔታ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በሰሜን ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ በማስመልከት ለአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ የሰላም እና የፀጥታ ኮሚሽነር ገለፃ አድርገዋል።
በገላጻቻም፤ ከፌደራል መንግስትና ህወሓት አመራሮች ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመቋጨት የሚያስችሉ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሲያደረጉ መቆየታቸውንም አስታውቋል።
የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አክለውም፤ “በኢትዮጵያ ጉዳይ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማበጀት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ቅንጅትና መደጋገፍ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
ኦባሳነጆ ገለጻ ባደረጉበት ስብሰባ ላይ የአፍሪካ የሰላምና የፀጥታው ምክር ቤት የየካቲት ወር ፕሬዝዳንት የሆኑት የኬንያዋ ተወካይ ጄን ካማው እና የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ የሰላም እና የፀጥታ ኮሚሽን ሊቀመንበር ባንኮል አዴዌ ተገኝቷል።
እንደ ኦባሳንጆ ሁሉ በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ ወደ ሰሙን ኢትዮጵያ ሄደው ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከጉብኝት በኋላ መግለጫ የሰጡትና በኢትዮጵያ ጉዳይ አዲስ ነገር ይኖር እንደሆነ የተጠየቁት አሚና መሐመድ፤ “በኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካ መሪዎች ጭምር ሰላምን በተመለከተ ከመንግስት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸው” አስታውቋል።
ከዚህ ባለፈም የሰላም ንግግሮች መቀጠላቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ ከወራት በፊት ከነበረው አንጻር አሁን ግጭቱ መቀነሱን አንስተዋል፡
ብሄራዊ ምክክሩ በራሱ ወደ ሰላም የሚወስድ ነውም ብለዋል የተመድ ምክትል ዋና ፀሀፏ አሚና መሀመድ።
በመንግስት በሽብር ወንጀል የሚፈለጉት የህወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ከሳምንታት በፊት ከመንግስት ጋር ንግግር መጀመሩን ቢገልጹም፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ከህወሃት ጋር የተጀመረ ንግግር እንደሌለ ለአል ዐይን ኒውስ መግለጻቸው ይታወሳል።