የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ከአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን ጋር መቀሌ ገብተዋል
በኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት የሚከታተለው የአፍሪካ ህብረት የታዛቢዎች ቡድን መቀሌ ገባ።
ታዛቢ ቡድኑ መቀሌ ሲደርስ የህወሓት ሊቀ መንብር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል አቀባል አድርገውላቸዋል።
የአፍሪካ ህብረት የታዛቢዎች ቡድን በመቀሌ ቆይታውም በሰላም ስምምነቱ የተጠቀሱ ነጥቦች ተፈጻሚነታቸውን የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ ከዚህ ደቀም መገለጹ ይታወሳል።
በተያያዘ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በመንግስት እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የጋራ የክትትል እና የማረጋገጫ ሥርዓትን በይፋ ለማስጀመር መቀሌ ገብተዋል።
ኢጋድ በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ዳግም ያረጋግጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢጋድ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ገልጿል።
በኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት የሚከታተለው የአፍሪካ ህብረት የታዛቢዎች ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት በናይሮቢ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።
በመግለጫውም የሁለቱም ወገኖች የጦር አዛዦች በናይሮቢ ተገናኝተው የትግራይ ሃይሎች ትጥቅ የሚፈቱበት፣ ወደ ካምፕ ገብተው ስልጠና ወስደው ዳግም ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን አስታውቋል።
- የፌደራል መንግስትና የህወሓት አመራሮች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መቀሌ ላይ ተገናኝተው ይመክራሉ ተባለ
- የመከላከያ ሰራዊት በመቀሌ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ስራ በዚህ ሳምንት ይከናወናል- አምባሳደር ሬድዋን
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም በመግለጫው ላይ የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን በሰላም ስምምነቱ የተጠቀሱ ነጥቦች ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ በጥቂት ቀናት ውስጥ መቀሌ ይገባል ማለታቸውም አይዘነጋም።
በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው ግጭት የማቆምና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስምምነት ሁለት ወራት ሞልቶታል። የስምምነቱ ማስፈጸሚያ ሰነድም በኬንያ ናይሮቢ ከተፈረመ ሰነባብቷል።
የትግራይ ሃይሎች ከበርካታ የጦር ግንባሮች መውጣታቸውን ካሳወቁ ቀናት ቢቆጠሩም እስካሁን ትጥቅ አልፈቱም። ለዚህም ህወሃት በምክንያትነት የሚጠቅሰው የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ አለመውጣትን ነው።
በዚህም የፌደራሉ መንግስት ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ሙሉ በሙሉ ተባባሪ አይደለም የሚል ወቀሳን የትግራይ ክልልን ከሚያስተዳድረው ህወሃት ይደመጣል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በተደረሰው የሰላም ስምምነት የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድር እና ሳያንጠባጥብ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ማሳወቁ ይታወሳል።
በያዝነው ሳምንትም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ የፌደራል መንግስ ልዑክ ወደ መቀሌ ማቅናቱም አይዘነጋም።