መንገደኞችን ያሳፈረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መቀሌ አርፏል
አየር መንገዱ ወደ ትግራይ ክልል ኤርፖርቶች አቋርጦት የነበረውን በረራ ዛሬ ጀምሯል
የፌደራል መንግሥት እና ህወሀት የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት በመመለስ ላይ ናቸው
መንገደኞችን ያሳፈረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መቀሌ አሉላ አባነጋ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል።
ይህም ከ19 ወራት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የትግራይ ቴሌቪዥን ባወጣው መረጃ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል ኤርፖርቶች አቋርጦት የነበረውን የመንገደኞች በረራ ዛሬ እንደሚጀምር ማሳወቁን ተከትሎ የትኬት ቢሮዎች ተጨናንቀዋል።
የናፈቋቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለማየት የጓጉ የትግራይ ተወላጆች በአየር መንገዱ የትኬት መሸጫ ጣቢያዎች ረጃጅም ሰልፎችን ይዘው ቢጠባበቁም ማስተናገድ የተቻለው የተወሰኑትን ነው።
አየር መንገዱ ከፍላጎቱ ጋር ያልተመጣጠነውን አገልግሎት ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታውቋል።
የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎቱ ሲስተካከል በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ በረራዎችን ለማድረግ ስለመዘጋጀቱም ነው የተገለጸው።
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በረራ ጀመረ
በሰሜን ኢትዮጵያ በህወሀት እና የፌደራል መንግሥቱ አማካኝነት ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ነበር አየር መንገዱ መደበኛ በረራውን ያቋረጠው።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው በዚህ ጦርነት የባንክ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችም የሀገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌ ገብቶ ከቆየባቸው ጥቂት ወራት በስተቀር አገልግሎቶቹ ተቋርጠው ቆይተዋል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ በተደረሰ ስምምነት መሰረት ህወሀት እና የፌደራል መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል።
ይሄንን ስምምነት ተከትሎም መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች ዳግም በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
ከነዚህ መካከልም አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን ከዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም ከአዲስ አበባ መቐለ መደበኛ በረራውን የጀመረበት ተጠቃሽ ነው።
ከትናንትናው በስቲያ በአፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌደራል መንግሥት ልዑካን ወደ መቀሌ አምርቶ ከተለያዩ አመራሮች እና የህዝብ ወኪሎች ጋር ተወያይቶ መመለሱ ይታወሳል።
በውይይቱ ወቅትም የባንክ፣ ትራንስፖርት ፣ ቴሌኮሙንኬሽን እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ መቅረቡ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ የጀመረው በረራም የሰላም ስምምነቱ አንዱ ትሩፋት ሆኗል።
ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመርም የፌደራል ተቋማት ሰራተኞች በመቀሌና አካባቢው የተለያዩ ስራዎችን እየከወኑ ነው ተብሏል።