የተመድ ዋና ፀሃፊ በኢትዮጵያ ዳግም ግጭት ዜና መደንገጣቸውን አስታውቀዋል
በኢትዮጵያ ሁኔታ “የደነገጡት” የተመድ ዋና ጸሃፊ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ ተደርሶ የነበረው ተኩስ አቁም “በአስቸኳይ” ወደ ነበረበት እንዲመለስ አሳሰቡ፡፡
ጉቴሬዝ በዛሬው እለት በተካሄደው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ጎን ለጎን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት መቀስቀሱ ዜና በመስማታቸው በጣም ማዘናቸውን እና መደግጣቸውን አስታውቀዋል።
“ኢትዮጵያውያን፣ ትግራዋይ፣ አማራች፣ ኦሮሞዎች፣ አፋሮች ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል” ያሉት ጉቴሬዝ፤ ግጭቱ ባስቸኳይ እንዲቆም፤ እንዲሁም በመንግስት እና በህወሓት መካከል የተጀመረው የሰላም ድርድር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለወራት ቆሞ የነበረውን ጦርነት መጀመሩን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ህወሓት ዛሬ ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሰራዊትና እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃይሎች ትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ባለው ግንባር በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቋል፡፡
የህወሓት መግለጫን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በዛሬው እለት ጠዋት 11 ሰዓት በተያየ አቅጣጫ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡
የፌደራል መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው ህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት ማስታወቁ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚደረደር መግለጹ ይታወሳል፡፡ ህወሓትም በተመሳሳይ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡