የአፍሪካ ሕብረት፤ የፌዴራል እና የኦሮሚያ ባለስልጣናት በቁጥር አናሳ ዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቁ አሳሰበ
ግድያው ተጣርቶ ተጠያቂነት እንዲሰፍንም ነው ህብረቱ ያሳሰበው
ህብረቱ በወለጋ የተገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ጉዳይ እንዳሳሰበው አስታውቋል
የአፍሪካ ሕብረት፤ የፌዴራል እና የኦሮሚያ ባለስልጣናት በቁጥር የአናሳ ብሔረሰቦችን እና አናሳ ዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቁ አሳሰበ፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በኦሮሚያ ክልል በተከሰቱና እየተከሰቱ ባሉ የዜጎች ጭፍጨፋ ዙሪያ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ኮሚሽን ሊቀመንበሩ የኦሮሚያ እና የፌዴራል መንግስታት በክልሉ የሚኖሩ በቁጥር አናሳ የሆኑ ዜጎችን ደህንነት እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡
የኦሮሚያ እና የፌዴራል መንግስታት በክልሉ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት መጠበቅ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ሙሳ ፋኪ እነደዚህ አይነት ድርጊቶችን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፤ በኦሮሚያ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ግድያ በአፋጣኝ ምርመራ እንዲደረግበትምም ነው በመግለጫው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
አህጉራዊው ተቋም ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነትን፣ አንድነትን፣ ሰላምንና እርቅን ከሚያቀነቅኑ ኃይሎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡
በግድያው የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹት ሊቀመንበሩ ከኢትዮጵያውያን ጎን መቆማቸውን አሳውቀዋል፡፡
በግድያው ጉዳይ ላይ የመከረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከደቂቃ የህሊና ጸሎት የዘለለ ተግባር እንዲፈጽም በአባላቱ ተጠይቋል፡፡
በዚህም ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማብራሪያ ለመስጠት እንደሚገኙ በሚጠበቅበት የነገ ሃሙስ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ/ም ስብሰባው ብሔራዊ የሃዘን ቀንን እንደሚያውጅ ይጠበቃል፡፡