ከደቂቃ የህሊና ጸሎት በዘለለ ሃዘኑ በብሔራዊ ደረጃ ሊገለጽ የሚችልበት ሁኔታ እንደሚቻች የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል
የሀገሪቱን ሕጎች በማመሳከር በቀጣይ ብሔራዊ የሃዘን ቀን ሊታወጅ እንደሚችል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
የም/ቤቱ አባላት በኦሮሚያ ክልል በዜጎች ላይ በተፈጸመው ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ ምክንያት ብሔራዊ የሃዘን ቀን እንድታወጅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የምክር ቤት አባላት በዜጎች ጭፍጨፋ ምክንያት በመላ ሀገሪቱ የሀዘን ቀን መታወጅ እንዳለበት ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
አባላቱ ከአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በዘለለ ሃዘኑ በብሔራዊ ደረጃ ሊገለጽ በሚችልበት መልኩ ብሔራዊ የሃዘን ቀን ሊታወጅ እንደሚገባ ዛሬ በነበረው ስብሰባም ጠይቀዋል፡፡ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ በምክር ቤት ጥያቄ ያነሱት የተቃዋሚም የገዥም ፓርቲ ተወካዮች ናቸው፡፡
አባላቱ ተጠያቂነት እንዲኖርም አጽንዖት ሰጥተው ጠይቀዋል፤ ምክር ቤቱ ለማቋቋም ያሰበው አጣሪ ኮሚቴ ተጨባጭና መሬት የወረዱ ስራዎችን ሊሰራ እንደሚገባ በመጠቆም፡፡
ጭፍጨፋዎች በተፈጸሙባቸው አካባቢዎች ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት ጉዳይ በወጉ ሊጤን እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
ምክር ቤቱ ወለጋ ላይ የተገደሉ ዜጎችን ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲይዝ በአብን አባላት የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ
አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ ብሔራዊ የሀዘን ቀንን ለማወጅ “ሕጎችን አይተን እንወስናለን” ማለታቸውም ነው የተገለጸው፡፡ አፈጉባዔው ጥያቄውን ውድቅ እንዳላደረጉት ይልቁንም ሕጎችን በማየት እንደሚተገበር መግለጻቸውንም ነው የመረጃ ምንጮቹ ያሉት፡፡
አፈጉባዔው “ያሉ አዋጆች ስላሉ ህጎቹን አይተን በሚቀጥለው ጊዜ እንወስናለን፤ ይህንን የምናደርገው ከህግ ጋር እንዳይጣረስብን ነው፤ ዛሬ ህጉ ይፈቅድልናል ወይስ አይፈቅድልንም የሚለውን ማየት አለብን” ማለታቸውን አባላቱ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነገ በወቅታዊ ጉዳዮችና በበጀት ዙሪያ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ሊታወጅ እንደሚችልም ነው የሚጠበቀው፡፡
የዜጎች ጭፍጨፋን ተከትሎ ብሔራዊ የሃዘን ቀን ከታወጀ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባ፤ መገናኛ ብዙኃን መደበኛ መርሃ ግብር ያቋጣሉ፤ የኢትዮጵያ አውሮፕላኖችና መርከቦች፣ በውጭ የሚገኙ ሚሲዮኖች ሰንደቅ ዓላማን ዝቅ አድርገው ያውለበልባሉ፡፡