አሜሪካ፣ብሪታኒያ እና አውስትራሊያ ወታደራዊ ጥምረት ለመፍጠር የሚያስችላቸውን እቅድ ይፋ አደረጉ
ሀገራቱ፤ “በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩት መርከቦች በፓስፊክ ቀጠና ለማሰማራት” ከስምምነት ደርሰዋል
መርከቦቹ በባህር ውስጥ ሰው አልባ ተሸከርካሪዎችን በማሰማራት ቅኝት ማድረግና በስውር ተልእኮ መፈጸም የሚችሉ ናቸው ተብሏል
አሜሪካ፣ብሪታኒያ እና አውስትራሊያ በ2023 ወታደራዊ ጥምረት ለመፍጠር የሚያስችላቸውን እቅድ ይፋ አደረጉ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “በአሜሪካ፣ በብሪታንያ እና በአውስትራሊያ መካከል የተደረሱና በቅርብ ጊዜ ይፋ የሚደረጉ የትብብር እና የደህንነት ዝግጅቶች አሉ” ብለዋል፡፡
“በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩ መርከቦች በፓስፊክ ቀጠና ለማሰማራት” በማለም የተፈጠረው ጥምረት የህንድ እና የፓሲፊክ ውቅያኖስ ቀጠናን ነጻ፣ ክፍት እና የተረጋጋ ማድረግን ግቡ ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የፕሬዝዳንቱን ሃሳብ የሚጋሩት ወታደራዊ ልሂቃንም እንዲሁ መርከቦቹ በፓስፊክ ቀጠና ያለውን የሃይል ሚዛን ለማስጠበቅ እንደሚያግዙ ይናገራሉ።
ዋይት ሃውስ ይዞት በወጣው የሶስቱም ሀገራት የጋራ መግለጫ እንደሚያትተው ከሆነ አውስትራሊያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያም ሆነ ዩራኒየምን ላለማበልጸግ ቁርጠኛ ናት፡፡
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልቤንዝ ፤ ሀገራቸው በአሜሪካ በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ የባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመግዛት መስማማቷን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በአውስትራሊያ ታሪክ ውስጥ “ ትልቁ ወታደራዊ ኢንቨስትመንት” ሊባል በሚችል መልኩ ዘመናዊ የባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመገንባት ፕሮጄክት ቀርጻ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
"ከአሜሪካ እና ከብሪታንያ ጋር የተደረገው ስምምነት አውስትራሊያ የመከላከያ አቅሟን ለመገንባት በታሪኳ የምታደርገው ትልቁ ኢንቨስትመንት ነው" ሲሉም ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኒኔዝ ፤በካሊፎርኒያ ሳንዲያጎ ከአሜሪከው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ከብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ፡፡
አውስትራሊያ ከአሜሪካ እና ብሪታንያ የምታገኛቸው መርከቦች በባህር ውስጥም ሰው አልባ ተሸከርካሪዎችን በማሰማራት ቅኝት ከማድረግ ባለፈ አወዛጋቢ በሆኑ የውሃ ክልሎችም በስውር ተልዕኳቸውን ፈጽመው የመመለስ ብቃት እንዳላቸው ይነገራል፡፡
የአሁኑ የሶስቱም ሀገራት ስምምነት ባሳለፍነው አመት ፈረንሳይን ከምዕራባውያን ወዳጆቿ ጋር እንድትጋጭ ምክንያት የሆነ ጉዳይ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
12 መርከቦችን በ62 ቢሊየን ዶላር ከፈረንሳይ ልትገዛ የነበረችው አውስትራሊያ ባለቀ ሰአት ስምምነቱን በድንገት አፍርሼዋለሁ ማለቷ ፓሪስን ከምዕራባውያን ወዳጇቿ ጋር ማነታረኩ የሚታወስ ነው፡፡
እንደ ፈረንሳይ ሁሉ ቻይና የሀገራቱን ስምምነት በጥበቅ ከሚቃወሙት ሀገራት ሆና ብቅ ብላለች፡፡
መርከቦቹ ለቁጥጥር የማይመቹና “አደገኛ” ናቸው ያለቸው ቤጂንግ፤ በሂደት ወዳልተፈለገ ግጭት ሊከት የሚችል ስምምነት እንዳይሆን ያለትን ስጋት ገልጻለች፡፡