አውስትራሊያ ከአሜሪካ የምትገዛቸው የጦር መርከቦች የፓስፊክን የሃይል ሚዛን ይለውጡት ይሆን?
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልቤንስ ዛሬ በአሜሪካ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ይመክራሉ
ካንቤራ በ2021 ስምንት በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩ የጦር መርከቦችን ከዋሽንግተን እና ለንደን ለመግዛት ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል
ፈረንሳይን ከምዕራባውያን ወዳጆቿ ጋር በጥቅም ያጋጨው የአውስትራሊያ የጦር መርከቦች ግዥ ዳግም መነጋገሪያ እየሆነ ነው።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልቤንስ ዛሬ በዋሽንግተን ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በሚያደርጉት ምክክርም ይሄው ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።
አውስትራሊያ ከፈረንሳይ በ62 ቢሊየን ዶላር ልትገዛ የነበረውን የጦር መርከብ ስምምነት በድንገት አፍርሼዋለሁ ማለቷ ፓሪስን ማስደንገጡ አይዘነጋም።
12 በነዳጅ ሃይል የሚሰሩ የጦር መርከቦችን ከፈረንሳይ ልታገኝ የነበረችው ካንቤራ፥ ስምንት በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩ መርከቦችን ከአሜሪካ እና ብሪታንያ ለመግዛት ተስማምቻለሁ ማለቷን ምዕራባውያኑን በጥቅም ማጋጨቱም የሚታወስ ነው።
ሀገራቱ የስምንቱ የጦር መርከቦች ሽያጭ ዝርዝር ውል እስካሁን ይፋ አላደረጉም።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር የአሜሪካ ጉብኝትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በቀጣይ ሳምንት በጋራ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
“ዘንዶዎቹ” እጅግ ፈጣንና ከእይታ ውጭ ረጅም ኪሎሜትሮችን መጓዝ የሚችሉ ናቸው።
በባህር ውስጥም ሰው አልባ ተሸከርካሪዎችን በማሰማራት ቅኝት ማድረግና ሚሳኤሎችን ጨምሮ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን የመሸከምም አቅም እንዳላቸው ይነገራል።
እነዚህ የጦር መርከቦች አወዛጋቢ በሆኑ የውሃ ክልሎችም በስውር ተልዕኳቸውን ፈጽመው መመለስ ይችላሉ ነው የተባለው።
በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩት መርከቦች በፓስፊክ ቀጠና ያለውን የሃይል ሚዛን ለማስጠበቅ እንደሚያግዙ ተንታኞች ይናገራሉ።
ከፓሪስ በመቀጠል ስምምነቱን የተቃወመችው ቻይና ለቁጥጥር የማይመቹትን የጦር መርከቦች “አደገኛ” ብላቸዋለች፤ የሶስትዮሹን ስምምነት በቅርበት እየተከታተለችው መሆኑንም አስታውቃለች።
ሲድኒ ታይምስ ትናንት “ቻይና እና አውስትራሊያ በ2026 ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ” የሚል ዘገባን ይዞ በወጣ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አልቤንስ የህንድ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ዋይትሃውስ ይዘልቃሉ።
ከጦር መርከብ ግዥው ባለፈ ካንቤራ 40 ሄሊኮፕተሮችን በ2 ቢሊየን ዶላር ለመግዛት መወሰኗ የፓስፊክ ቀጠናን ውጥረት ይበልጥ እንዳይጨምረው ተሰግቷል።