አውስትራሊያ አሜሪካና ፈረንሳይን በመሳሪያ ሽያጭ ግጭት ውስጥ ከተተች
ካንቤራ የፓሪስ “ታይፓን” ሄሎኮፕተሮች ለጥገና ወጪያቸው ከፍ ያለ ነው በሚል 40 ሄሊኮፕተሮችን ከአሜሪካ ለመግዛት ወስናለች
አውስትራሊያ ከፈረንሳይ በ62 ቢሊየን ዶላር ልትገዛ የነበረውን የጦር መርከብ ስምምነት ማፍረሷና ወደ አሜሪካ ማዘንበሏ ፓሪስ እና ዋሽንግተንን ማነታረኩ ይታወሳል
አውስትራሊያ አሜሪካና ፈረንሳይን በመሳሪያ ሽያጭ ግጭት ውስጥ ከተተች
አውስትራሊያ ከአሜሪካ በ2 ቢሊየን ዶላር ሄሊኮፕተሮችን ለመግዛት መወሰኗን አስታወቀች።
ካንቤራ የፓሪስ “ታይፓን” ሄሎኮፕተሮች ለጥገና ወጪያቸው ከፍ ያለ ነው፤ የመለዋወጫ እቃዎችም አይገኙም የሚል ምክንያትን በማቅረብ ፊቷን ወደ ዋሽንግተን አዙራለች።
ይህም ከ2021 ወዲህ የሻከረውን የፈረንሳይና አውስትራሊያ ግንኙነት ይበልጥ ችግር ውስጥ እንዳይከተው ተሰግቷል።
የአውስትራሊያ መከላከያ ሚኒስትር ሪቻርድ ማርለስ ግን የሄሊኮፕተር ግዥው “ከፓሪስ ጋር እያደስነው ያለውን ግንኙነት አያሻክረውም” ሲሉ ተደምጠዋል።
የፈረንሳይ መንግስት “ታይፓን” የተሰኙትን ሄሊኮፕተሮች የሚያመርተው ኤርባስ ኩባንያ ላይ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ አለው።
ኤርባስ “የአውስትራሊያን ውሳኔ አከብራለሁ” ያለ ሲሆን ሀገሪቱ አሁንም ዋነኛ የገበያ መዳረሻው እንደምትሆን ገልጿል።
የኤሊዜ ቤተመንግስት ሹማምንት ግን የካንቤራን ውሳኔ በበጎው እንደማይመለከቱት ነው የሚጠበቀው።
አውስትራሊያ አንቶኒ አልቤንዝ ባለፈው አመት ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከፈረንሳይ ጋር ግንኙነቷን ለማደስ ሙከራ ማድረግ ብትጀምርም ዛሬ ይፋ ያደረገችው ውሳኔ ለፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር መልዕክቱ ግልጽ ነው ይላል አሶሼትድ ፕረስ።
አውስትራሊያ ከፈረንሳይ በ62 ቢሊየን ዶላር ልትገዛ የነበረውን የጦር መርከብ ስምምነት በድንገት አፍርሼዋለሁ ማለቷ ፓሪስን ማስደንገጡ አይዘነጋም።
12 በነዳጅ ሃይል የሚሰሩ የጦር መርከቦችን ከፈረንሳይ ልታገኝ የነበረችው ካንቤራ፥ ስምንት በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩ መርከቦችን ከአሜሪካ እና ብሪታንያ ለመግዛት ተስማምቻለሁ ማለቷንም ፈረንሳይ በክህደት ነው የተመለከተችው።
ሀገራቱ ፓሪስን ገለል አድርገው የሶስትዮሽ የደህንነት ስምምነት ተፈራርመናል ማለታቸውም የፈረንሳይን ሹማምንት ክፉኛ ማበሳጨቱን ፍራንስ 24 አስታውሷል።
አሁን ደግም የፈረንሳይን “ታይፓን” ሄሊኮፕተሮች በአሜሪካዎቹ “ብላክ ሃውክ” ሄሊኮፕተሮች ለመተካት የተላለፈው ውሳኔ የጥቅም ፍጥጫውን እንደሚያንረው ተንታኞች ይገልጻሉ።