አውስትራሊያ ከቻይና ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷ አይቀርም የተባለው ለምንድን ነው?
የአውስትራሊያ የደህንነት ባለሙያዎች ሀገራቱ ከሶስት አመት በኋላ ጦር ሊማዘዙ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል
የካንቤራ ወታደራዊ ዝግጁነት ግን እጅግ አሳሳቢ ነው ያሉት የደህንነት ባለሙያዎቹ፥ ሀገራቱን ወደ ጦርነት የሚያስገቡ ምክንያቶች አብራርተዋል
አውስትራሊያ ከቻይና ጋር ጦር ልትማዘዝ እንደምትችል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን የሀገሪቱ የደህንነት ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ሲድኒ ሞርኒንግ ጋዜጣ ዛሬ ይዞት በወጣው ዘገባ፥ የሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ጦርነት በ2026 ሊጀመር እንደሚችል አመላክቷል።
ጋዜጣው አምስት ከፍተኛ የደህንነት ባለሙያዎችን አነጋግሮ ያጠናቀረው ዘገባ ሁለቱን ሀገራት ወደ ጦርነት ሊመሩ የሚችሉ ምክንያቶችን አስቀምጧል።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ቻይና በቅርቡ በታይዋን ላይ ወታደራዊ እንደምትወስድ ይጠበቃል።
ይህም ለታይፒ ድጋፏን በተለያየ መንገድ የገለጸችውን አሜሪካ እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮቿን ወደ አውስትራሊያ እንድትልክ ሊያደርጋት ይችላል ነው የሚሉት ገለልተኛ የደህንነት ጉዳይ አማካሪ ባለሙያዎቹ።
በዚህም ምክንያት ቤጂንግ በካንቤራ ለይ የሚሳኤልም ሆነ የሳይበር ጥቃቶችን በማድረስ ጦርነቱ ሊጀመር እንደሚችልም በመጥቀስ።
አውስትራሊያ ባለፈው አመት ከፈረንሳይ ጋር የገባችውን ውል ሰርዛ ከአሜሪካ እና ብሪታንያ በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩ የጦር መርከቦች ግዥ መፈጸሟ ይታወሳል።
ይህ የሶስትዮሽ ጥምረት በፓስፊክ ቀጠና ምን ይዞ እንደሚመጣ በባለሙያዎቹ ባይብራራም ካንቤራ የጦር አውድማ እንድትሆን አንዱ ምክንያት እንደሚሆን ግን ተጠቅሷል።
የአለማችን የጦር መሳሪያ ክምችት በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት እየተመናመነ መምጣት እና የምዕራባውያን ሙሉ ትኩረት ኬቭ ላይ መሆኑም ለአውስትራሊያ አደገኛ ነው ተብሏል።
በአንጻሩ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የሀገሪቱን ጦር የሚገነቡበት ፍጥነት ቆም ብሎ ማሰብና በፍጥነት የወታደራዊ ዝግጁነትን ማጠናከር እንደሚገባ የሚያሳስብ ስለመሆኑ መናገራቸውም በሲድኒ ሞርኒንግ ጋዜጣ ተጽፏል።
ባለሙያዎቹ ያለፉት አስር አመታት የአውስትራሊያ ዝግጅት “የጤና አይደለም” ሲሉም ሞግተዋል።
የአንቶኒ አልቤንዝ መንግስት ባለፈው አመት የሀገሪቱ መከላከያ ሃይል ዝግጁነት እንዲጠና ሲያዙ የተገኘው ውጤት ሀገሪቱ ለሚቃጣባት ጦርነት ምላሽ ለመስጠት በጥቂቱ 10 አመት የዝግጅት ጊዜ ያስፈልጓታል የሚል ሆኗል።
ቻይና እና አውስትራሊያ ጠንካራ የንግድ ግንኙነት የመሰረቱ ሀገራት ናቸው።
አውስትራሊያ አምስተኛዋ የቻይና የገቢ ንግድ ምንጭ ስትሆን፥ 10ኛዋ የቻይና የወጪ ንግድ መዳረሻ ናት።