አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያን አገደች
አውስትራሊያ ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያ እዳይጠቀሙ የሚከለክል ህግ በማጽደቅ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች
በአዲሱ ህግ እነ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራምና ቲክቶክ ታዳጊዎችን ከገጻቸው ካልከለከሉ 32 ሚሊየን ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል
የአውስትራሊያ መንግሥት ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት የትኛውንም ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግድ ሕግ አጸደቀ።
የአውስትራሊያ ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት “ለመከላከል” ያለመ ነው የተባለለት አወዛጋቢው ህግ በትናንትናው እለት በአውስትሊያ ፓርላማ ቀርቦ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ጸድቋል።
በዓለማች የመጀመሪያው ነው የተባለለት አዲሱ የአውስትሊያ ህግ ለግዙፎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ነገሮች የሚያከብድ ሲሆን፤ ለሌሎች መንግስታት ደግሞ እንደ መነሻ እንደሚሆን ተነግሮለታል።
ህጉ ፌስቡክና ኢንስታግራምን የሚያስተዳረው ሜታ ኩባንያ፣ ቲክቶክ እንዲሁም ሌሎች የማህራዊ ሚዲያዎች ህጻናት ወደ ገጻቸው እንዳይገቡ የማይከለክሉ ከሆነ 49.5 ሚሊየን የአውስትራሊያ ዶላር ወይም 32 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ የሚያስገድድ ነው።
ህጉን በሙከራ ደረጃ ከጥር ወር ጀምሮ መተግር ይጀምራል የተባለ ሲሆን፤ እግዳው በአንድ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተነግሮለታል።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔስ በዛሬው እለት በህጉ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት “ማህራዊ ሚዲያዎች አሁን የልጆቻችንን ደህንነት የማረጋገጥ ማህበራዊ ሃላፊነት አለባቸው” ብለዋል።
“የማህበራዊ ሚዲያ ጉዳይ ለእናቶች እና ለአባቶች ስቃይ ሆኖ ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ይህ ሕግ ለአባቶች እና ለእናቶች ነው” ሲሉም ተግናርዋል።
የማህበራዊ ሚዲያ እገዳዉን ተከትሎ በአውስትራሊያውን ዘንድ የተደበላለቀ ስሜት ተፈጥሯል የተባለ ሲሆን፤ ህጉ መጽደቁ ጥሩ ነገር ነው፤ አንዳነዴ ህጻናት ማየት የማይገባቸውን ነገር ያያሉ፤ ስለዚህ እገዳው ተገቢ ነው ያሉ ነዋሪዎች አሉ።
የሲድኒ ነዋሪ የሆኑት የ58 አመቱ ሾን ክሎዝ "በጣም ተናድጃለሁ፣ ይህ መንግስት ዲሞክራሲን በመስኮት አውጥቶ እንደጣለው ይሰማኛል" ብለዋል።