‘ባካልቾ’ የተሰኘው የሲዳምኛ ጋዜጣ በሀዋሳ ተመረቀ
“ጋዜጣው የሲዳማን ቋንቋና ባህል ከማጎልበት ባለፈ የእውነተኛ ፌዴራሊዝም ማሳያ ነው”- የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር

ኢፕድ የሚያሳትመው ባካልቾ ጋዜጣ በሳምንት አንድ ጊዜ ታትሞ ለንባብ የሚቀርብ ነው
‘ባካልቾ’ የተሰኘው የሲዳምኛ ጋዜጣ በሀዋሳ ከተማ ተመረቀ
80ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሲዳምኛ እና ትግርኛ ህትመት የጀመረ ሲሆን ‘ባካልቾ’ የተሰኘውን የሲዳምኛ ጋዜጣውን ዛሬ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አስመርቋል።
ንጋት የሚል ትርጓሜ ያለው ባካልቾ ጋዜጣ ፣ የሲዳማ ህዝብ በክልል ለመደራጀት ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ህዝበ ውሳኔ ባደረገ በዓመቱ ነው ለምርቃት የበቃው።
በምረቃው ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ፣ ክልሉ በተመሰረተ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፕሬስ ድርጅት በሲዳምኛ ህትመት መጀመሩ ለቋንቋው እድገት እንዲሁም የሲዳማን የተለያዩ ባህሎች እና ሁለንተናዊ ማንነት ለማስተዋወቅና ለማጎልበት ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
የሲዳማ የማንነት ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ በሀገር አቀፍ የህትመት ሚዲያ ደረጃ በቋንቋው ህትመት መጀመሩ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እውነተኛ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ የመሆኑ ማሳያ እንደሆነም ነው አቶ ደስታ የገለጹት፡፡
የክልሉ መንግስት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል በመግለጽ የሲዳማ ህዝብም ጋዜጣውን በማንበብ ለዕድገቱ አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ተደራሽነትን ለማሳደግ ካለው ራዕይ በመነሳት ድርጅቱ በ80ኛ ዓመት የልደት በዓሉ የሲዳሚኛ እና የትግርኛ ጋዜጦችን ማሳተም መጀመሩን የተናገሩት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ጌትነት ታደሰ ፣ የሲዳማ ክልል ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎች ቋንቋዎች ህትመት ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁንም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እንደሚያበረታታ የገለጹት የባለስልጣኑ ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ለዚህም ተቋሙ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡
ሲዳሚኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ባካልቾ ጋዜጣን ከማንበብ ባለፈ የሥነ-ጽሁፍ ስራዎችን በማበርከትም ሊሳተፉ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ባካልቾ የተሰኘው በሲዳሚኛ ቋንቋ የሚታተመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጣ በየሳምንቱ ሀሙስ እለት እየታተመ ለንባብ እንደሚቀርብ ተገልጿል፡፡
ጋዜጣው በሀዋሳ ከተማ ሀይሌ ሪዞርት በተመረቀበት በዛሬው ዕለት ለገበያ ቀርቦ መሸጥም ጀምሯል፡፡