ቢቢሲ 400 ገደማ የሚሆኑ ሰራተኞቹን ከስራ ሊያሰናብት መሆኑን አስታወቀ
ቢቢሲ አዲስ ባስቀመጠው የዲጂታል ስርጭት እቅድ በአመት ውስጥ 500 ሚሊዮን ፓውንድ ለማትረፍ ማቀዱ ተገልጿል
ቢቢሲ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ 1 ሺህ ሰራተኞችን የመቀነስ እቅድ እንዳለው ሲገልጽ ቆይቷል
የብሪታኒያው ብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ቢቢሲ) ወጪ ለመቆጠብና ወደ ዲጂታል ሚዲያ ለመሸጋገር በሚል 400 ገደማ መሆኑ ሰራተኞቹን ከስራ እንደሚሰናብት አስታወቀ፡፡
ከተመሰረተ 100 ዓመት የሞላው የእንግሊዙ ብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ቢቢሲ) በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ 1 ሺህ ሰራተኞችን የመቀነስ እቅድ እንዳለው ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ቢቢሲ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የሀገሪቱ መንግስት የሚያደርግለትን የበጀት ድጎማ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንደሚያቋርጥ ማሳወቁን ተከትሎ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም መሰረት ቢቢሲ ወጪ ለመቆጠብ በሚል 382 ሰራተኞቹን ሊሸኝ መሆኑ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ወጪ በሚቀንስ መልኩ የሚያስተላልፋቸው ፕሮግራሞች ወደ ዲጂታል ፕላትፎርሞች ስርጭት በማሸጋገር የአድማጭ ተመለካቾቹን ፍላጎት ለማሟላት ይሰራልም ነው የተባለው፡፡
ቢቢሲ እቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ከ41 የቋንቋ አገልግሎቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወደ ዲጂታል አገልግሎት የሚቀየሩ ይሆናል፡፡
ከዚህ በፊት ቢቢሲ ወርልድ ኒውስ እና ቢቢሲ ኒውስ ቻናል በሚል ለየብቻ ሲሰራጩ የነበሩ ሚዲያዎችን ባንድ ላይ በማድረግ በበይነ መረብ በመታገዝ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት መወሰኑም ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም ቢቢሲ ራዲዮ አራት በመባል ሲሰራጭ የነበረው የመደበኛ ስርጭት ቀርቶ በኢንተርኔት እንዲሰራጭ ተወስኗልም ተብሏል፡፡
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ ከወራት በፊት ለሰራተኞቻቸው ባደረጉት ንግግር ቢቢሲ ከጊዜው ጋር እንዲራመድና የሚሰጠውን የይዘት ስርጭት አግልግሎት እንዲቀጥልበት ከተፈለገ “ሪፎርም መደረግ አለበት” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የሰራተኛ ቅነሳው በዴቪ የተቀመጠው "ዲጂታል-መር" የሚዲያ ድርጅት እውን የማድረግ እቅድ አካል ነው ተብሏል፡፡
ቢቢሲ 75 በመቶ ተከታዮቹን በአዲሱ ቢቢሲ አይፕሌየር(BBC iPlayer) በኩል የመድረስ እቅድ እንዳለውም አስታውቋል፡፡
ቢቢሲ አዲስ ባስቀመጠው የዲጂታል ስርጭት መሰረት በአንድ ዓመት ውስጥ 500 ሚሊዮን ፓውንድ ለማትረፍ ያሰበ ሲሆን በቀጣይም በዲጂታል መሰረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ማድረጉን እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጿል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት እና ዓለማችን ቢቢሲ ወደ ዲጂታል ስርጭቶች እንዲገቡ ይፈልጋሉ ያሉት ስራ አስኪያጁ ከዚህ በፊት ያልታዩ የዲጂታል ሚዲያ የስርጭት መንገዶችን እንደሚከተልም አክለዋል፡፡
በፈረንጆቹ 1922 የተመሰረተው ቢቢሲ እንግሊዝ በዓለም ላይ ለተጫወተችው ዓለም አቀፍ ፖለቲካ ትልቁን አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ይነገራል፡፡