ጋዜጠኛ ታምራት የማነን ጨምሮ በትርጁማንነት ሲሰሩ ነበር የተባሉት ፍጹም ብርሃኔ እና አሉላ አካሉ ከግርማይ ጋር መታሰራቸው ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል
መቀሌ በሚገኙ የጸጥታ አካላት ተይዟል የተባለለት የቢቢሲ የመቀሌ ዘጋቢ ግርማይ ገብሩ ከእስር መፈታቱን ቢቢሲ አስታወቀ፡፡
የትግሬኛ ዘጋቢው ግርማይና 4 ባልደረቦቹ ከነበሩበት ካፍቴሪያ በወታደራዊ አካላት መወሰዱን የአይን እማኞችን ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲ በነጻ መለቀቁንም አስታውቋል፡፡
ጋዜጠኛ ታምራት የማነን ጨምሮ በትርጁማንነት ሲሰሩ ነበር የተባሉትን ፍጹም ብርሃኔ እና አሉላ አካሉ ከእስር መለቀቃቸውንም ነው የዘገበው፡፡
ፍጹም ብርሃኔ ኤኤፍፒ ለተባለው ዓለም አቀፍ ሚዲያ በተርጓሚነት ይሰራ እንደነበር ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡ ባሳለፍነው አርብ መቀሌ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በወታደራዊ አካላቱ መወሰዱን ቤተሰቦቹ አረጋግጠውልኛልም ብሏል፡፡
አሉላ አካሉ ደግሞ ለፋይናንሺያል ታይምስ ነው በአመቻችነት ይሰራ የነበረው፡፡ ሆኖም ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ዩኒፎርም የለበሱ ሶስት ወታደሮች እና አንድ ሲቪል በከተማይቱ ከሚገኝ አንድ ሬስቶራንት ወስደውታል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው፡፡
ተርጓሚ ናቸው የተባሉትን ጨምሮ የጋዜጠኞቹ መታሰር እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የሃሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ተደጋጋሚ ፈተናዎችን ቢደቅኑም ጋዜጠኞችን ማሰሩ የሚመጥን አይደለም ያለው ኮሚሽኑ ተጨባጭነት ያለው ክስ እንዲመሰረትባቸው አለበለዚያም በነጻ እንዲለቀቁ መጠየቁም አይዘነጋም፡፡