የአማራ ልዩ ኃይልን በመጥቀስ በአሜሪካ የተሰጠው መግለጫ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራ መሆኑን ኢትዮጵያ ገለጸች
ሚኒስቴሩ የትግራይ ክልልን የሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ ደጋግሞ ከማለቃቀስ ይልቅ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ… አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት ብሏል
“አስፈላጊውን የጸጥታ መዋቅር በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ማሰማራት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መብት ነው" ውጭ ጉ/ሚኒስቴር
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ የካቲት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስበው አስታውቋል፡፡
በትግራይ ክልል ያልተገደበ የሰብአዊ አገልግሎት መፈቀዱን እና መንግስት ለመብት ጥሰት ምርመራዎች ዓለም አቀፍ ድጋፍን ለመቀበል መዘጋጀቱን አሜሪካ በበጎ እንደምትቀበልም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ ለማሻሻል ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም ሰዎች ለመድረስ ከዓለም ዓቀፍ አጋሮች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም የጠቀሰ ሲሆን እስካሁን በክልሉ ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በመንግስት የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው 30 በመቶ በልማት አጋሮችና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መሸፈኑን ነው የጠቆመው፡፡
እስካሁን ድረስ በክልሉ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደደረሳቸውም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ መንግስት በአሁኑ ወቅት የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በክልሉ ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀዱንም መግለጫው አስታውሷል፡፡
“በዚሁ መሰረትም የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢስሌይ ምንም እንኳን ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም ለሰብዓዊ ቀውሱ እየተሰጠ ያለው ምላሽ እየተሻሻለ መምጣቱን አረጋግጠዋል” ነው ያለው መግለጫው፡፡ ሚኒስቴሩ አክሎም የክልሉን አስከፊ የሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ ደጋግሞ ከማለቃቀስ ይልቅ የተጀመረውን የእርዳታ ሥራ ለማጠናከር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጨማሪ ድጋፍ በማድረግ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ዜጎቹን ደህንነት ለመጠበቅ ኃላፊነቱን በቁም ነገር ይወስዳል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡ ለዚህም ነው መንግስት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት እና በትግራይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሔድ በመፍቀድ ለሁለት ዐቢይ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠው ሲል ገልጿል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን እ.ኤ.አ. የካቲት 27/ 2021 በሰጡት መግለጫ ወቅት የተነሱ ናቸው፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫቸው የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ መውጣት እንዳለባቸውም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና ይህ ሀሳባቸው በኢትዮጵያ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የሚኒስትሩን ንግግር “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መግለጫ የመስጠት ሙከራ ፣ በተለይም የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በመጥቀስ በብሊንከን የተሰጠው መግለጫ የሚያሳዝን ነው” በማለት ተቀባይነት እንደሌለው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
“እንደዚህ አይነት ጉዳዮች የኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊነቶች ብቻ መሆናቸው ሊታወቁ ይገባል” ያለው መግለጫው፣ እንደ ሉዓላዊ ሀገር አስፈላጊውን የጸጥታ መዋቅር ሕግ ለማስከበር በሚፈልግባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የማሰማራት ኃላፊነት እንዳለው አስገንዝቧል።
እንደማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር የኢትዮጵያ መንግስትም በፌዴራልና በክልል መዋቅሩ ውስጥ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ተጠያቂ የሚሆንባቸው ተቋማዊ መርሆች እንዳሉትም ጠቅሷል፡፡
መግለጫው አክሎም “የፌዴራል መንግስቱ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ሲኖር ሰላምና ጸጥታን የማስፈን ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነት አለበት” ብሏል። የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ያካሔደው በተጠቀሰው ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነት እና የሀገሪቱን አንድነት ከከፋፋይ ኃይሎች በመጠበቅ መንፈስ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፍ ኃላፊነቷን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗን የጠቀሰው መግለጫው ይህ ግን “ሉዓላዊ በሆነችው ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ለማዘዝ እንደመጋበዝ ተደርጎ በማንኛውም አካል ሊቆጠር አይገባም” ብሏል፡፡