ሩሲያ እና ዩክሬን ዛሬ በቱርክ ያደረጉት ውይይት ካለስምምነት ተጠናቋል
ቤላሩስ፤ በሩሲያ ላይ የሚቃጣ የትኛውንም ጥቃት እንደምትመክትና እንደምትከላከል የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ለመከላከያ መስሪያ ቤታቸው፤ የቤላሩስ ጦር ሩሲያ የሚሰነዘርባትን ጥቃት መከላከል እንደሚገባው መናገራቸውን የሀገሪቱ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡ የቤላሩስ ጦር ከዩክሬን በኩል የሚሰነዘርና ሩሲያን የሚያጠቃ ኃይልን መመከት እንደሚገባው ፕሬዝዳንቱ ለመከላከያ ኃላፊያቸው መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡
የሩሲያን የአቅርቦት መስመሮች ለመቁረጥ በድፍረት የሚነሳ እና ሩሲያን ሊያጠቃ የሚችል ኃይልን ቤላሩስ መከላከል እንደሚገባትም ነው ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ያስታወቁት፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቤላሩሱ አቻቸው አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ነገ እንደሚገናኙ እየተጠበቀ ነው፡፡ ዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት እንኳን የሞስኮ እና ሚኒስክ ወዳጅነት በአደባባይና በተግባር እየታየ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ ምዕራባውያን ሩሲያ በዩክሬን እያደረገችው ያለው ጦርነት “ወረራ” ነው እያሉ እየከሰሷት ሲሆን አንዷ ተወቃሽም ቤላሩስ ናት፡፡
ቤላሩስ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ምክንያት ማዕቀቦች እየተጣሉባት ነው፡፡
ጦርነት ላይ ያሉት ዩክሬንና ሩሲያ ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻው አማካኝነት በቱርክ የሪዞርት ከተማ አንታልያ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ ወይይቱ ግን አልተሳካም ተብሏል፡፡
በሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና በዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ መካከል በቱርክ የተካሄደው ውይይት ያለ ስምምነት ተጠናቋል ተብሏል፡፡