በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ሁለት ሚሊዮን ደረሰ
እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ያህሉ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል ተብሏል
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረች 11ኛ ቀን ሆኗታል
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ሁለት ሚሊዮን መድረሱ ተገለጸ፡፡የሩሲያ ጦር ወደ ዩክሬን ግዛት ገብቶ ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው ጦርነት 11ኛ ቀኑን ይዟል፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ መካረር ገብታ አሁን ላይ ወደ ይፋዊ ጦርነት ውስጥ ከገባች አስራ አንድ ቀናት ሆኗታል፡፡
የሩሲያ ጦርም የዩክሬን ድንበር አልፎ ዋና ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር በሂደት ላይ ነው፡፡
ሁለቱ ሀገራት ለተጎጂዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በሚል በተወሰኑ ከተሞች ጊዜያዊ የተኩስ አቁመው ቢያውጁም ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፤ ተኩስ አቁሙን በመጣስ ሁለቱ ሀገራት እየተካሰሱ ነው፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ዩክሬናዊያን ዜጎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን ማለፉን የተመድ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁት ወደ ጎረቤት ሀገራት ማለትም ወደ ፖላንድ፣ ሞልዶቫ፣ ሮማንያ፣ስሎቫኪያ፣ ሩሲያ እና ሀንጋሪ ተሰደዋል ተብሏል፡፡
ቀሪዎቹ ተፈናቃዮች ደግሞ በዩክሬን ውስጥ ባሉ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ጦርነቱን ብቻዬን እየተዋጋሁ ነው የምትለው ዩክሬን ኔቶ የሀገራቸውን የአየር ክልል እንዲዘጋ ብትጠይቅም ኔቶ ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ በዩክሬን ጉዳይ የትኛውም ሀገር ጣልቃ እንዳይገባ አስጠንቅቃ የዩክሬን መሪዎች በዚሁ ከቀጠሉ ዩክሬን ሀገርነቷን ልታጣ ትችላለች ብላለች፡፡
የሩሲያ ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ "በዩክሬን ያለው ጦራችን በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተልዕኮውን በሚገባ እየፈጸመ ነው፣ በዩክሬን መስራት ያለብንን ስራዎች ሁሉ እያከናወኑ ነው" ብለዋል ፡፡
የምእራባዊያን ሀገራት በሩሲያ ጦር ላይ የሚነሱ ዜናዎች ሁሉ መሰረት የሌላቸው ተራ ፕሮፓጋንዳዎች ናቸው ያሉት ፕሬዘዳንቱ የዩክሬን ጦር ስደተኞች እና ንጹሃን ዜጎችን እንደ መያዣ እየተጠቀመ መሆኑንም አክለዋል፡፡