የፑቲን ወዳጅ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ “ዩክሬን በእኛ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀች ነው” ሲሉ ከሰሱ
ሉካሼንኮ ከዩክሬን የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከት ወታደሮች አሰማርተናል ብለዋል
የቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገር የነበረችው ቤላሩስ በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን የቆመች ብቸኛዋ ሀገር ናት
የፑቲን የቅርብ ወዳጅ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ “ዩክሬን በእኛ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀች ነው” ሲሉ ከሰሱ፡፡
ሉካሼንኮ ከሀገሪቱ የደህንነት ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ "ዛሬ ዩክሬን እየተወያየች ብቻ ሳይሆን በቤላሩስ ግዛት ላይ ጥቃት ለማድረስ እቅድ እንዳላት አስቀድሜ ተናግሬያለሁ" ማለታቸውም ነው ቤልታ የተሰኘው የመንግስት የዜና ወኪል የዘገበው።
አክለውም "የሩሲያ ፌዴሬሽን እና የቤላሩስ ሪፐብሊክ ጥምር ጦር ለማሰማራት ተስማምተናል" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ሉካሼንኮ ወታደሮቹ የት ቦታና አቅጣጫ እንደሚሰማሩ ግን በግልጽ ያሉት ነገር የለም።
ጥምር ጦሩ ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ በዝግጅት ላይ እንዳለ ያስረዱት ሉካሼንኮ መቼም ቢሆን ራስን መካለከል የሚቻለው ወተዳረዊ አቅምን ማጠናከር ሲቻል መሆኑም ተናግረዋል፡፡
“ሰላም ከፈለግክ ለጦርነት መዘጋጀት አለብህ" ሲሉም ነው የተደመጡት፡፡
ቤላሩስ “ወደ ጦርነት ሊጎትቱን የሚሞክሩትን ሁሉንም ዓይነት ተንኮለኞች ለመከላከል የሚያስችል እቅድ ሊኖራት ይገባል”ም ብለዋል፡፡
ቤላሩስ በፋይናንሺያል እና በፖለቲካዊ መልኩ በዋና አጋሯ ሩሲያ ላይ እንደምትመካ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ "በቤላሩስ ግዛት ላይ ጦርነት ሊኖር አይገባም" ሲሉም የደህንነት ሾሞቻቸውን አሳስበዋል፡፡
ፕሬዝዳንተ ሉካሼንኮ ሞስኮ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከመጀመሯ በፊት በነበሩት ወራት ውስጥ በወታደራዊ ልምምድ ሰበብ የሩሲያ ወታደሮችን ወደ ቤላሩስ እንዲገቡ የፈቀዱ መሪ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡
ከጦርነቱ በኋላም ቢሆን በሩሲያ ላይ የሚቃጣ የትኛውንም ጥቃት ቤለሩስ እንደምትመክትና እንደምትከላከል በአደባባይ በመናገር ለፑቲን ያላቸው አጋርነት ያረጋገጡባቸው በርካታ አጋጠሚዎች ይታወሳሉ፡፡
የቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገር የነበረችው ቤላሩስ ከዩክሬን ጋር ባለው ጦርነት ከሩሲያ ጎን ከቆሙ ሀገራት መካከል ብቸኛዋ ናት፡፡
ከቤላሩስ ውጪ ሁሉም የቀድሞዎቹ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገራት ከሩሲያ በተቃራኒ ወይም ከምዕራባዊያን ጎን ተሰልፈው የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን የምዕራባዊያንን ማዕቀብንም በማስፈጸም ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
እናም ቤላሩስ የዩክሬን ኢላማ ልትሆን የምትችልበት ትልቅ እድል እንዳለ ይነሳል፡፡