አብን አቶ መልካሙ ሹምዬንም ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በለጠ ሞላን (ዶ/ር) በድጋሚ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።
አቶ መልካሙ ሹምዬ ደግሞ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።
ፓርቲው ለሦስት ቀናት ሲያካሂድ በቆየው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው የሥራ አስፈፃሚ አባላቱን በአዲስ በማደራጀት ማጠናቀቁን የፖርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጣሂር መሐመድ ገልጸዋል።
በአዲሱ አደረጃጀት መሰረትም የሳይንስ እና የኢኖቬሽን ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ሊቀመንበር፣ አቶ መልካሙ ሹምዬ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የፓርቲው የቀድሞውና የመጀመሪያው ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)ም የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ዩሱፍ ኢብራሒም የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ በመሆን ተሾመዋል፡፡
የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት አቶ ክርስቲያን ታደለ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ክፍል ኃላፊ፤ እንዲሁም የአደረጃጀት ኃላፊ የነበሩት አቶ ጋሻው መርሻ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነዋል፡፡
የቀድሞው ጋዜጠኛ አቶ ጣሂር መሐመድ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነታቸው ቀጥለዋል፡፡
የድርጅቱን የውጭ ግንኙነት ይመሩ የነበሩት ቴዎድሮስ ኃይለማርያም (ዶ/ር) በጽህፈት ቤት ኃላፊነት እንዲሁም አቶ ሐሳቡ ተስፋዬ በአደረጃጀት ጉዳዮች ኃላፊነት ተሾመዋል፡፡
በአዲስ መልክ ከተዋቀረው አብን የሥራ አስፈፃሚዎች መካከል 3ቱ አዲስ መሆናቸውን አሚኮ ዘግቧል። የፖርቲው 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤም በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ተጀምሯል።
አብን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የውስጠ ፓርቲ ችግሮች እንደገጠሙት እየተነገረ ይገኛል፡፡ በጉባዔው እነዚህን ችግሮች ለመሻገር የሚያስችል ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
አብን በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)ን እና አቶ ክርስቲያን ታደለን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ማስመረጡ ይታወሳል፡፡
ሊቀመንበሩን በለጠ ሞላ (ዶ/ር)ን ጨምሮ አቶ ዩሱፍ ኢብራሒም እና አቶ ጣሂር መሐመድ በተለያዩ የመንግስት ኃላፊነቶች ተሾመው በማገልገል ላይ መሆናቸውም አይዘነጋም፡፡