"መንግስት በአሸባሪነት የተፈረጀውን ድርጅት ቁንጮ አመራሮች ከእስር በመፍታት ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል" - አብን
ውሳኔውን የተቃወመው የንቅናቄው ስራ አስፈፃሚ ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል
ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ማብራሪያ የተፈጸመ ነው ያለው ውሳኔ የሀገርና የህዝብን ጥቅምና ክብር በፅኑ እንደሚጎዳም አብን አስታውቋል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግስት "ቁንጮ" ናቸው ያላቸውን የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መፍታቱን ተቃወመ።
የአብን ስራ አስፈጻሚ ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫው መንግስት በአሸባሪነት የተፈረጀውን ድርጅት ቁንጮ አመራሮች ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ማብራሪያ ከእስር በመፍታት የሀገርና የህዝብን ጥቅምና ክብር በፅኑ የሚጎዳ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል ብሏል፡፡
ውሳኔው ለሀገር ህልውናና ለህዝባችን ሰላምና ደህንነት በመላው ኢትዮጵያውያን የተከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ የሚያሳጣ፤ በይቅርታና "በሰብአዊነት ስም የተፈፀመ "ኢ-ሰብአዊና ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ ነው ብሎ እንደሚያምንም ነው የገለጸው።
እንዲህ ዓይነቱ "ግብታዊና ኢ-ፍትሃዊ" ውሳኔ በመንግሥት ህጋዊና ሞራላዊ መሰረት ላይ እየጎሉ የመጡትን ክፍተቶች የሚያረጋግጥ፣ በመንግሥትና በህዝብ መካከል በየጊዜው እየጨመረ የመጣው ርቀትና ያለመተማመን የሚያጎላ መሆኑን እንደሚገነዘብም ገልጿል፡፡
ከሁሉም በላይ አመፅንና አመፀኞችን የሚሸልምና ሰላማዊና ህጋዊ ፖለቲካን ክፉኛ የሚጎዳ ውሳኔ በመሆኑ በአፋጣኝ እርምት እንዲያገኝ ሲልም ጠይቋል፡፡
አብን አስቸኳይና ትኩረት የሚሹ ናየው ያላቸውን ጉዳዮችንም በተመለከተ ያለውን አቋምም በመግለጫው ግልጽ አድርጓል።
ጦርነቱ በአሸናፊነት እንደተደመደመና የህልውና አደጋው እንደተቀረፈ መስተጋባቱ ከእውነታው የተጣረሰና ህዝብን የሚያዘናጋ ነው ያለ ሲሆን መንግሥት ካለፉ ስህተቶቹ ተምሮ ተቀዳሚ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ሲል አሳስቧል፡፡
ህዝቡ ለአፍታም ቢሆን ሳይዘናጋ በሁሉም አውደ ግንባሮች የሚያደርገውን ፍልሚያ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቋል፡፡
የጅምላ ጥቃት በህዝባችን ላይ ቀጥሏል ያለው አብን "ከትግራይ ወራሪ ኃይል ጋር በተናበበና በተቀናጀ መልኩ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የቀጠሉ የጅምላ ግድያና ማፈናቀል ድርጊቶች እንዲቆሙ ፤ በተለይ በወለጋና በሸዋ ደራ በኦነግ/ሸኔ አማካኝነት የሚፈፀመው ግልፅ ወረራ አስቸኳይ ምላሽ እንዲያገኝ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ሃላፊነታቸውን ይወጡ ሲል አሳስቧል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ትህነግና ኦነግ/ሸኔን" አስመልክቶ ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊነቱን እንዲቆጣጠርም ጠይቋል፡፡
በጦርነቱ የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ መገንባቱ ተገቢውን ትኩረት አላገኘም ያለም ሲሆን ይደር የማይባልና ከህልውና ጦርነቱ አደማደም ጋር በጥምረት ሊሰራ የሚገባው መሆኑን ገልጿል።
የአማራና የአፋር ህዝብ በተለይ ከመላው ኢትዮጵያውያን፣ ከማዕከላዊ መንግሥትና ከአቻ ክልሎች ልዩ ትኩረትና ድጋፍ እንዲያገኙም ጠይቋል፡፡
ንቅናቄው በመግለጫው በህልውና ትግሉ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት የአማራና የአፋር የፀጥታ ኃይሎች የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴው አንድ የትኩረት ማዕከል ሆነው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቋል።
በተለይም ለአማራ ፋኖዎች ከአጉል የፖለቲካ ፍረጃ በፀዳ ምልከታ ተገቢው ክብርና እውቅና ሊሰጣቸው ሊደገፉም ይገባል ያለም ሲሆን በቀጣይ የትብብር ስልት ተዘርግቶለት የህዝብና የሀገር የደህንነት ጋሻ ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲመክሩና እንዲሰሩም አሳስቧል፡፡
የታሰበው ሃገራዊ ምክክር ግልፅ፣ አካታችና ተአማኒ መሆናቸውን ፤ የችግራችንን የስር መንሥኤዎች ማስተናገዳቸውን ፤ የምክክር ሂደቱም ግልፅ ኃላፊነት የተሰጠው ፣ በተገቢ አወቃቀር ፣ ህግጋትና ሥርዓተ ደንብ መመራቱን ለማረጋገጥ የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸም ሲሆን የአማራን ህዝብ ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በምክክሩ ተገቢውን ውክልና እና ጉልብትና (empowerment) እንዲያገኙ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጧል።
ሁሉም አካላት በአንድነት አሸባሪና አጥፍቶ ጠፊ ኃይሎችን በማያዳግም ሁኔታ እንዲደመስሱም ጥሪ አቅርቧል፡፡