ጆ ባይደን፤ አሜሪካ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታወቁ
ድጋፉ የአሜሪካ ኮንግረስ በግንቦት ወር ያጸደቀው የ40 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አካል ነው ተብሏል
ዩክሬናውያን ሰቆቃ ውስጥ ናቸው ያሉት ጆ ባይደን የሀገሪቱ ሉዓላዊነት የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ቃል ገብተዋል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፤አሜሪካ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታወቁ፡፡
ጆ ባይደን ሀገራቸው ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ በዩክሬን የነጻነት ቀን ይፋ ማድረጋቸው፤ ዩክሬናውያን ከሩሲያ ጋር እያደረጉት ባለው ጦርነት አሜሪካ የዩክሬን ትግልን ለመርዳት ያላትን ቁርጠኝነት እየቀጠለ ለመሆኑ ማረጋገጫ እንደሆነም ነው ኤኤፍፒ የዘገበው፡፡
የተሰጠው ድጋፍ ዩክሬን ፤በአየር መከላከያ እንዲሁም የመድፍ ስርዓቶችና ጥይቶችን እንድታጎለብት ብሎም ከረዠም ርቀት ጥቃቶች እራሷን መከላከል እንደምትችል ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ አመላክቷል፡፡
ድጋፉ አሜሪካ በተናጠል በጦርነትው ውስጥ ላለችው ለዩክሬን ካደረገችው ድጋፍ ትልቁ ነው ተብሎለታል፡፡
በኮንግረስ ይሁንታ ባገኘውና በሀገራቱ መካከል በሚደረገው የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር መሰረት አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን ያደረገችው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው፡፡
በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ወታደራዊ እርዳታ የአሜሪካ ኮንግረስ በግንቦት ወር ያጸደቀው የ40 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አካል ነው ተብሏል።
ጆ ባይደን የዩክሬን ህዝብ ከፍተኛ ሰቆቃ ላይ ነው ያለው መግለጫው ፤ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ቃል ገብተዋል።
"በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ እንዲሁም ሌሎች ብዙዎች የሩሲያ ግፍና ጥቃት ሰለባ ሆነዋል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ነገር ግን ዩክሬናውያን ላለፉት ስድስት ወራት ባደረጉት ተጋድሎ በሀገራቸው ኩራት እንዲሰማቸው ከማሰቻል በዘለለ 31ኛው የነጻነት በዓላቸው ማክበር ችለዋል”
ሲሉም አክለዋል
ጆ ባይደን አሜሪካ ለውጊያ ወደ ዩክሬን የምትልከው ወታደር እንደማይኖር ነገር ግን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡