“ሌላ የዓለም ጦርነት አንፈልግም” - የአሜሪካ ጦር ጠቅላይ አዛዥ
ጠቅላይ አዛዡ አውሮፓ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮቹ በኃያላኑ መካከል ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል
ለሩሲያ ወረራ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ለመመከት የሚያስችል አቅም እንዳለን ማሳየት አለብንም ብለዋል
“ሌላ የዓለም ጦርነት” እንደማትፈልግ አሜሪካ አስታወቀች፡፡
የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄነራል ማርክ ሚሌይ “ሌላ የዓለም ጦርነት አንፈልግም” ሲሉ አውሮፓ ለሰፈሩ አሜሪካ ጦር አባላት ተናግረዋል፡፡
በሩሲያ ዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት 13ኛ ቀን ማስቆጠሩን አስመልከተው ለጦር አባላቱ ንግግር ያደረጉት ጦር አዛዡ ወታደሮቹ በኃያላኑ መካከል ሌላ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ጄነራል ማርክ የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን እና የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዲሁም የሃገሪቱ የመከላከያ እና የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ዋና ወታደራዊ አማካሪ ናቸው፡፡
ሃገራቸው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆኑ የምስራቅ አውሮፓ ሃገራትን ከሩሲያ ወረራ እንደምትጠብቅ ማረጋገጫ ለመስጠት የሚያስችል ጉብኝትን በማድረግም ላይ ይገኛሉ፡፡
በደቡባዊ ሩማኒያ የሰፈሩ የአሜሪካ ጦር አባላትንም ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ባደረጉት ንግግርም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያለንን ጥናካሬ፣ ቁርጠኝነት እና አጋሮቻችንን ከሩሲያ ወረራ ለመጠበቅ እንዲሁም በኃያላኑ መካከል ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ለማድረግ የሚያስችል አቅም እንዳለን ማሳየት አለብን ብለዋል፡፡
በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ከ150 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወት መቀጠፉን በመግለጽም ይህ እንዲደገም አንፈልግም ብለዋል ጄነራሉ፡፡
አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ የተለያዩ ሃገራት የተሰማራ 67 ሺ ገደማ ጦር አላት፡፡
ከዚህ ውስጥ 2500 ያህሉ የባልቲክ ሃገራት በሆኑት በሉትዋኒያ፣ ላቲቪያ እና ኢስቶኒያ የተሰማሩ ናቸው፡፡ 10 ሺ ያህሉ በፖላንድ የሰፈሩም ሲሆን 2400 በሩማኒያ፣ 1500 በስሎቫኪያ፣ 350 በቡልጋሪያ እንዲሁም 200 ያህሉ ደግሞ በሃንጋሪ የሰፈሩ ናቸው፡፡
አሜሪካ መቀመጫውን ጀርመን ያደርጋል ያለችውን ጦር ወደ አውሮፓ እንደምትልክ ፕሬዝዳንት ባይደን መናገራቸውም ይታወሳል፡፡
የኔቶ በምስራቃዊ አውሮፓ መስፋፋት እና የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት አካል የነበሩ ሃገራትን አባል ማድረግ ብሔራዊ ስጋትን ደቅኖብኛል በሚል መስፋፋቱ እንዲቆም ደጋግማ ስታሳስብ የነበረችው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት ሁለት ሳምንታትን ማስቆጠሩ ይታወቃል፡፡