ዋሽንግተን የሃውሲ አማጽያንን የሽብር ድርጊት አውግዛለች
የሃውሲ አማጽያንን ተከታታይ ጥቃቶች ተከትሎ አሜሪካ ጸረ ሚሳዔል መርከቦችን ጨምሮ ተዋጊ የጦር ጄቶችን ወደ ዩኤኢ ልትልክ ነው
የአሜሪካ መከላከያ ጸሃፊ ኦስቲን ሊሎድ ከአቡ ዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ እና ዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ በስልክ ካወሩ በኋላ ነው ዋሽንግተን ይህን ለማድረግ የወሰነችው፡፡
በስልክ ቆይታቸው ጥቃቱን ያወገዙት ኦስቲን ሊሎድ ዩኤኢ ከእንዲህ ዐይነት ጥቃቶች ራሷን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዙ ለልዑል አልጋ ወራሹ ነግረዋቸዋል፡፡
ከሃገሪቱ ባህር እና አየር ኃይል ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩ ጸረ ሚሳዔል የጦር መርከብ እና ተዋጊ የጦር ጄቶችን ወደ ዩኤኢ አሰማራለሁም ነው መከላከያ ጸሃፊው ያሉት፡፡
ሃገራቸው ከዩኤኢ ጎን እንደምትቆም ግልጽ አድርገው መናገራቸውንም ነው ጽህፈት ቤታቸው ያስታወቀው፡፡
ከሰሞኑ አማጽያኑ ወደ አቡዳቢ ያስወነጨፉት ተከታታይ የሚሳዔል ጥቃት በዩኤኢ ጦር ኃይሎች ከሽፏል፡፡
ሆኖም ንጹሃንንና የንጹሃንን መገልገያዎች ዒላማ ባደረገው የመጀመሪያ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉ እና ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ውግዘት ማስከተሉ ይታወሳል፡፡