ቻይና በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከሞስኮ ጋር ከወገነች 3ኛው የዓለም ጦርነት ይነሳል ሲሉ ዘለንስኪ አስጠነቀቁ
ቤጂንግ ለሩሲያ 'የመሳሪያ እርዳታ' ለመስጠት እያሰበች ነው መባሏን አጣጥላለች
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሚስጥር በዩክሬን ባደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት የአሜሪካን 'የማያወላውል' ድጋፍ ቃል ገብተዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ በሀገራቸው እየተካሄደ ባለው ጦርነት ቻይና ሩሲያን ብትደግፍ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ይጀመራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ቻይና በቀጠለው ግጭት ውስጥ ብትገባ መዘዙን ካስጠነቀቁ በኋላ ቤጂንግ ለሩሲያ 'የመሳሪያ እርዳታ' ለመስጠት እያሰበች ነው መባሏን አስተባብላለች።
"ለእኛ ቻይና በዚህ ጦርነት የሩሲያ ፌዴሬሽን አለመደገፏ አስፈላጊ ነው" ሲሉ ዘለንስኪ ለጀርመኑ ዲ ዌልት እለታዊ ጋዜጣ ተናግሯል።
"በእርግጥም ከጎናችን እንዲሆኑ እፈልጋለሁ። በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ የሚቻል አይመስለኝም። ቻይና እዚህ [ዩክሬን] ላይ እየሆነ ስላለው ነገር ተግባራዊ ግምገማ እንድታደርግ እድል አላት። ምክንያቱም ቻይና ከሩሲያ ጋር ብትተባበር የዓለም ጦርነት ይኖራል። እናም ቻይና ይህን የምታውቅ ይመስለኛል" በማለት የትብብር መዘዝን ገልጸዋል።
የዘለንስኪ ማስጠንቀቂያ የመጣው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሚስጥር በዩክሬንን ድንገተኛ ጉብኝት ባደረጉበት ቀን ነው።
ባይደን ከጦርነቱ አንደኛ ዓመት በፊት የ500 ሚሊዮን ዶላር አዲስ የጦር መሳሪያ አቅርቦት እና የአሜሪካን 'የማያወላውል' ድጋፍ ቃል ገብተዋል ሲል ዴይሊ ሜል ዘግቧል።
ጉብኝቱ የተካሄደው ፕሬዝዳንት ፑቲን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዩ ጋር ሊያደርጉት ከሚጠበቀው ውይይት በፊት ነው።