ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር ደርሳ ከነበረው ስምምነት መውጣቷን አስታወቀች
ፑቲን ሩሲያ የ“ኒው ስታርት ስምምነትን” ለማቋረጧ አሜሪካና የኔቶ አጋሮቿን ተጠያቂ አድርገዋል
ሩሲያና አሜሪካ አንድ ላይ 90 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የኒውክሌር ጦር ባለቤት መሆናቸው ይታወቃል
የሩሲው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ እና አሜሪካ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመቀነስ የተስማሙበትን “የኒው ስታርት ስምምነት” ተሳትፎዋን ማቋረጧን አስታወቁ፡፡
አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናት በቀሩት የዩክሬን ጦርነት ትልቅ ጫና ውስጥ የሚገኙት ፑቲን ይህን ያሉት በሀገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
“ሩሲያ የጦር መሳሪያ ገደብ የሚጥለውን ስምምነት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ማቋረጧን ዛሬ ለማሳወቅ እገደዳለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ፑቲን የሩሲያ የኒውክሌር ሃይል ኩባንያ ሮሳቶም አስፈላጊ ከሆነ ሀገሪቱ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለመሞከር ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጥ አለበት ሰሉም ትእዛዝ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
"በእርግጥ ይህን ለማድረግ የመጀመሪያዎቹ አንሆንም፤ አሜሪካ ሙከራ የምታደርግ ከሆነ ግን እናደርገዋለን" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ በስምምነቱ ያላትን ተሳትፎ ለማቋረጧ አሜሪካ እና የኔቶ አጋሮቿን ተጠያቂ ማድረጋቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ አጋሮቿ በዩክሬን ጦርነት "በእኛ ላይ 'ስልታዊ ሽንፈት' ሊያደርሱብን ይፈልጋሉ እንዲሁም በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ኒውክሌር ተቋሞቻችን ለመድረስ ይሞክራሉ" ሲሉም ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል፡፡
በተጨማሪም ፑቲን በስምምነቱ መሰረት አሜሪካ የሩስያ የኒውክሌር መስሪያ ቤቶችን ፍተሻ እንደገና እንዲጀምር ግፊት ስታደርግ፣ የኔቶ አጋሮቿ ዩክሬን የኒውክሌር አቅም ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ቦምቦችን በሚያስተናግዱ የሩሲያ አየር ሰፈሮች ላይ የድሮን ጥቃት እንድትሰነዝር ረድተዋታል ሲሉም ሞግተዋል።
"በዩክሬን ጥቅም ላይ የዋሉት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በኔቶ የባለሙያ እርዳታ የታጠቀቻቸውና ዘመናዊ ናቸው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አሁን የሩሲያ የመከላከያ ተቋማት እንመርምረት ማለታቸው ከንቱ ነውም ብለዋል፡፡
ነገር ግን ሩሲያ በስምምነቱ ያለትን ተሳትፎ ብታቆምም ሙሉ በሙሉ ከስምምነቱ እንዳልወጣች አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል ፕሬዝዳንት ፑቲን።
እንደፈረንጆቹ በ2010 በቼክ ረፐብሊኳ መዲና ፕራግ የተፈረመው ስምምነት ከ2011 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጀ-ባይደን በ2021 ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለአምስት አመታት መራዘሙ አይዘነጋም፡፡
ስምምነቱ አሜሪካ እና ሩሲያ ሊያሰማሯቸው የሚችሉትን ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች፣ በመሬት እና በባህር ሰርጓጅ ላይ የተመሰረቱ ሚሳይሎችን እና ቦምብ አውሮፕላኖችን ብዛት ላይ ገደብ የሚጥል መሆኑም ይታወቃል፡፡
ሁለቱም ኃያላን ሩሲያ እና አሜሪካ አንድ ላይ 90 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የኒውክሌር ጦር ባለቤት ናቸው፡፡
ሀገራቱ ያላቸው አቅም ፕላኔቷን ለማጥፋት በቂ እንደሆነም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡